ቀጥታ፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ እውን እንዲሆን የዜጎችን ክህሎትና እውቀት ማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት ይገባል

ጭሮ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ እውን እንዲሆን ዜጎች በዘርፉ ያላቸውን ክህሎትና እውቀት ማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ሀገር በቀል ክህሎትን በማጎልበት የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው

ስትራቴጂው የዲጂታል መሰረተ ልማት ዝርጋታን፣ የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽነትን፣ የዲጂታል ፋይናንስ መጠናከርን እና ዲጂታል የመንግስት አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግን ዓላማ አድርጎ እየተተገበረ ይገኛል። 

የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ስኬታማ ሊሆን የሚችለውም ዘርፉን በአግባቡ የተገነዘበ፣ በክህሎት እና በእውቀት የጎለበተ ዜጋ ሲገነባ መሆኑም ተመልክቷል።

ኢዜአ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር ቆይታ ያደረገ ሲሆን፤ ምሁራኑ የዲጂታል መሰረተ ልማትን ማስፋፋት የመንግስት አገልግሎቶች ግልጽ፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ እንዲሆኑ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።

ከዩኒቨርሲቲው ምሁራን መካከል አቶ ፈቃዱ ወርቁ እንደገለጹት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ የአገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን ባለፈ ዘመናዊ ከተሞችን በመፍጠር የዜጎችን አኗኗር ያቃልላል። 



ዘርፉ ለሀገር እድገት ከሚኖረው አስተዋጽኦ መካከል በቴክኖሎጂው ዘርፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንዲሁም የክፍያ እና የፋይናንስ ዘርፉን ማዘመን ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

በመሆኑም የዘርፉን ፋይዳ በአግባቡ ለመጠቀም በዲጂታል ቴክኖሎጂ በቂ ክህሎት እና እውቀት ያላቸው ዜጎችን ማፍራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሌላኛው የዩኒቨርሲቲው ምሁር አቶ ደርብ ገረመው በበኩላቸው፤ በተለይም የ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን በማስተሳሰር የዜጎችን ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል። 


 

በአሁኑ ወቅት ስራ ላይ የዋለው ዲጂታል መታወቂያ እና የመንግስት ተቋማት ወደ ዲጂታል አሰራር መሸጋገራቸው የዘርፉ ትልቅ እመርታ መሆኑን አንስተዋል። 

የተጀመረው የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ግቡን እንዲመታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በእውቀት እና በክህሎት ግንባታ ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም አክለዋል።

በ"ዲጂታል 2025" ስትራቴጂ የተመዘገቡ ስኬቶች ለ2030 ስትራቴጂ መሳካት ጠንካራ መሰረት እንደሚሆኑ የገለጹት ደግሞ አቶ ኢስማኤል ሁሴን ናቸው። 


 

በተለይም በፋይናንስ ዝውውር እና በግብይት ስርዓቱ ላይ የታዩ አዎንታዊ ለውጦች፣ እንዲሁም የከተማ ይዞታን በዲጂታል መለያ በማደራጀት ደህንነቱ የተጠበቀ ዳታ መገንባት መቻሉን እንደ ምሳሌ አንስተዋል። 

የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ዘመናዊና ፈጣን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት ምቹ መደላድል እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለቀጣይነቱም የክህሎት እና የእውቀት ግንባታ መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም