ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ስትራቴጂክ የማዕድን ሃብቶች በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል መሠረት እየተጣለ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 3/2018(ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያን ስትራቴጂክ የማዕድን ሃብቶች በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል መሠረት እየተጣለ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ ገለጹ።

የማዕድን ሚኒስቴር የምርመራ ፈቃዳቸውን አጠናቀው ወደምርት ለሚሸጋገሩ የወርቅ፣ የብረትና የፖታሽ አምራች ኩባንያዎች የምርት ፈቃድ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማምረት አቅምን በማሳደግ፣ ተኪና ወጪ ምርቶችን በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የፖታሽ ልማት፣ ዜድዋይቲቢ-ዲአይኤም ስቲል ማኑፋክቸሪንግ የብረት ልማት እንዲሁም ቤሮ ማይኒንግ በወርቅ ልማት ፍቃድ አግኝተዋል።


 

በዚህ ወቅት የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ፤ ኢትዮጵያ የማዕድን ሃብቶቿን በማልማት ለሀገር ዕድገት ማዋል የሚያስችል ትልቅ እርምጃ ወስዳለች ብለዋል።

የማዕድን ማምረት ስምምነትና ፈቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎችም ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ዋና ዋና ስትራቴጂክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ብረትን በሀገር ውስጥ ማምረት አለመቻሉ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድር መቆየቱን አውስተው፤ የዛሬው ስምምነት ይህን ችግር የሚፈታ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ የብረት ማዕድን ክምችት ያላት ሀገር ብትሆንም ምርቱን በማልማት ተጠቃሚ መሆን ሳትችል መቆየቷን አንስተዋል።

መንግስት ራሱ ፋይናንስ በማድረግ ማስጀመሩም በተለያየ ምክንያት ሲቋረጥ የነበረውን ብረት የማምረት ሂደት ወደተግባር መቀየሩን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።


 

በወርቅ ምርት የተሰጠው ፈቃድም የዘርፉን ምርታማነት በማዘመን ተጠቃሚነትን የበለጠ ማረጋገጥ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ያለውን የፖታሽ ሃብት ለማልማት በርካታ ሙከራ ቢደረግም እስካሁን የተገኘ ጥቅም እንደሌለ አስታውሰዋል።

በዚህም የመንግስትና የግሉን ዘርፍ አጋርነት በማጠናከር ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን ለማልማት አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የማዕድን ማምረት ፈቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎችም በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ የልማት ስራ በመስራት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም