ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማምረት አቅምን በማሳደግ፣ ተኪና ወጪ ምርቶችን በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 2/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማምረት አቅምን በማሳደግ፣ ተኪና ወጪ ምርቶችን በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡  

ሚኒስቴሩ የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄን ይበልጥ ለማስተዋወቅና የ2018 ኤክስፖውን ማስተዳደር የሚያስችል አዲስ ድረ-ገጽ ይፋ አድርጓል፡፡ 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡልልታ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል።  

በተለይም በኢንዱስትሪዎች የውድድር አቅም በማሳደግ፣ በማምረት አቅም እንዲሁም በተኪ ምርቶች ጥራትና መጠን ረገድ ከፍተኛ መሻሻሎች ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስምንት ወራት የኢንዱስትሪ ዘርፉ የወጪ ንግድ ምርት የ40 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የንቅናቄውን ተደራሽነት ለማስፋት እና መረጃዎችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማዳረስ የሚያስችል አዲስ ድረ-ገጽም ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።

የንቅናቄው አካል የሆነውና በየዓመቱ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ዘንድሮ “ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ገልጸዋል። 

ኤክስፖው ከሚያዝያ 24 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ጠቅሰው 270 የሚሆኑ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪዎች እንደሚሳተፉበትም ጠቅሰዋል። 

በዘንድሮው ኤክስፖ የተሳታፊዎች ምዝገባና ተያያዥ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ በዲጂታላይዜሽን የታገዙ እንደሚሆኑም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

ከኤክስፖው መጀመር በፊት የንቅናቄውን ዓላማ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ታላቅ የሩጫ ውድድር መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡ 

በዚህ ስፖርታዊ መርሃ ግብር ላይ ከ17 ሺህ በላይ ሯጮች እና 800 የሚጠጉ ታዋቂ አትሌቶች እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል፡፡ 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም