ቀጥታ፡

ተመዝግበን ካርድ የወሰድነው ለልማት ቅድሚያ የሚሰጥ ፓርቲን ለመምረጥ ነው

ወልቂጤ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተመዝግበው ካርድ የወሰዱት ለልማትና ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ለሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መሆኑን የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና እድገት ይበጃል ለምንለው ፓርቲ ድምጻችንን ለመስጠት የምርጫ ካርድ እየወሰድን ነው -ወጣቶች

በወልቂጤ ከተማ ምርጫ ክልል በሚገኙ 138 ምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል።

ኢዜአ በወልቂጤ ከተማ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፤ ተመዝግበን ካርድ የወሰድነው ለሀገሪቱ ልማትና ሰላም ቅድሚያ የሚሰጥ የፖለቲካ ፓርቲን ወደ ስልጣን ለማምጣት ነው ብለዋል ።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ አብድልማሊክ ሹሌ ፤ በምርጫው ለመሳተፍና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ይናገራሉ ።


 

ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ በመሆኑም በድምጻቸው ለሀገር ሰላምና እድገት ይበጃል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

የከተማው ነዋሪ ወጣት በለጠ ሀብቱ፤ በጠቅላላ ምርጫው ሀገርን ያሳድጋል ብዬ ያመንኩበትን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ወስጃለሁ ነው ያለው።


 

በተለይ የወጣቶች ስብእና ግንባታ ላይ ትኩረት የሚሰጥ፣ የስራ አጥነት ችግርን የሚፈታና አማራጭ የልማት ፖሊሲን ይዞ የሚቀርብ የፖለቲካ ፖርቲን ለመምረጥ መዘጋጀቱን አመላክቷል።

ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም በሀገራዊ ምርጫው ለመሳተፍ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን የገለፁት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አሰለፈች ይርጉ ናቸው።


 

የመምረጥና መመረጥ መብት በሕገ-መንግስቱ ለዜጎች የተሰጠ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው ያሉት ወይዘሮ አሰለፈች ሀገርን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሻግራል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወልቂጤ ምርጫ ክልል ስራ አስፈፃሚ አቶ ተገኑ ደመቀ፤ በምርጫ ክልሉ በሚገኙ 138 ምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በሁሉም ጣቢያዎች መራጮች ካርድ የሚወስዱት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው የዘንድሮው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓም የሚካሄድ ሲሆን ለዚሁ የሚሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም