ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና እድገት ይበጃል ለምንለው ፓርቲ ድምጻችንን ለመስጠት የምርጫ ካርድ እየወሰድን ነው -ወጣቶች

ጭሮ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና እድገት ይበጃል ለሚሉት ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት የምርጫ ካርድ እየወሰዱ መሆኑን በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የጭሮ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

በ"ምርጫዬ" መተግበሪያ አማካኝነት ባለንበት ሆነን የመራጭነት ካርድ መውሰዳችን ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም አስችሎናል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት ወር ላይ ለሚካሔደው ጠቅላላ ምርጫ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የመራጭነት ምዝገባ እየተካሔደ ነው።

ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ለአንድ ወር እንደሚቆይ የገለፀ ሲሆን  ዜጎች በምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ወይም "ምርጫዬ" የተሰኘውን መተግበሪያ በስልካቸው በመጫን መመዝገብ እንደሚችሉ አሳውቋል።

ኢዜአ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ በሚገኙ የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎች በመዘዋወር ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫ ካርድ የወሰዱ ወጣቶችን አነጋግሯል።

በከተማው ጨፌ አራራ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሰይፈ ዮሐንስ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ መብቴን መጠቀም የሚያስችለኝን ዕድል በማግኝቴ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል ብሏል።

በምርጫ ካርዱም ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና እድገት የሚበጅ እንዲሁም በሀገራዊ ልማቱ ወጣቶችን ይበልጥ አሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ለሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ድምጹን ለመስጠት መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ወጣት ፈልመታ ኢብራሂምም በተመሳሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ካርድ በማውጣት ልዩ ስሜት የሚፈጥር ሁነት በመሆኑ ደስታ ተሰምቶኛል ነው የሚለው።


 

በአሁኑ ወቅትም መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ ክርክሮችን በመከታተል ሀገሪቱን ወደ ተሻለ እድገት፣ ልማትና ብልፅግና ያሻግራል ብዬ ላመንኩበት ፓርቲ ድምጼን ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።

ምርጫ ለዜጎችና ለሀገር ለውጥ ልዩ ትርጉም ያለውና የወደፊት የአገሪቷን ጉዞ የሚወስን በመሆኑ ወጣቱ ህብረተሰብ በንቃት እንዲሳተፍም መልእክት አስተላልፏል።

የመራጭነት ካርድ ለመጀመሪያ ጊዜ መውሰዱም በምርጫው ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዳሳደረበት የሚናገረው ደግሞ ወጣት ነብሱ አሜን ነው።


 

በቀጣዩቹ አምስት ዓመታት ሀገሪቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ሁለንተናዊ ጥረት ያደርጋል ብዬ ላመንኩበት ፓርቲ ድምጹን ለመስጠት የሚያስችለኝን ዝግጅት እያደረግኩኝ ኑው ብሏል ።

ወጣት ሶና ተሾመ፤ አገሪቱ አሁን የደረሰችበትን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይ ለማድረግና በጠንካራ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ ለሚችል ፓርቲ ድምጼን ለመስጠት የመራጭነት ካርድ ወስጄያለሁ ሲል ገልጿል።


 

በአሁኑ ወቅት በከተሞች የሚያስፈልገውን ልማት የሚያስቀጥልና የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፓርቲን ወደ ስልጣን ለማምጣት ለመጀመሪያ ጊዜ በመራጭነት መመዝገቡን ነው የሚገልፀው።

ምርጫው ሰላማዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡም ወጣቶቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም