ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ አስደናቂ የልማት ስኬት ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የዘመናዊ ክትመት ፋና ወጊ እያደረጋት ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ አስደናቂ የልማት ስኬት ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የዘመናዊ ክትመት ፋና ወጊ እያደረጋት መሆኑን በአፍሪካ ሕብረት የሴቶች፣ ሰላምና ደኅንነት ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሊበራታ ሙላሙላ ገለጹ።

የኮሪደር ልማት ዘመናዊ ከተሜነትን በማስፋፋት ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል እያደረገ ነው

በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት የተገኙ አስደናቂ ስኬቶች መዲናዋን ውብ ገጽታ በማላበስ የዘመናዊ ክትመት ሥርዓትን እንድትከተል አስችሏታል።

የአዲስ አበባ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ የልማት ስኬቶችም አሁን ላይ በ70 የኢትዮጵያ ከተሞች ተስፋፍቶ አመርቂ የከተሜነት የልማት ውጤት እያስገኘ ነው።


 

አምባሳደር ሊበራታ ሙላሙላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በአዲስ አበባ የተገነቡ አስደናቂ የልማት ውጤቶች መዲናዋን የአፍሪካ የንግድና የባህል ማዕከል እያደረጋት ነው ብለዋል።

የመዲናዋ አስደናቂ የልማት ስኬቶችም ኢትዮጵያን አዲሲቷ የአፍሪካ ዘመናዊ የክትመት ሥርዓት ተምሳሌትና ፋና ወጊ የስልጣኔ ብርሃን እያደረጋት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመዲናዋ የተመዘገበው አስደናቂ የልማት ስኬትም የአዲስ አበባ ከተማን የአፍሪካ የለውጥ ማዕከልነት በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ የ24/7 የልማት መንገድም የኢትዮጵያዊያንን የአይበገሬነት መንፈስ በመግለጥና የሥራ ባህልን ለማዳበር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ አስደናቂ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ውብ ገጽታ መዲናዋን የአፍሪካ ማዕከል በማድረግ የኢትዮጵያን የዕድገት ትንሳኤ የሚያበስር መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአዲስ አበባ ዕድገት በአመራርና ህዝብ ቅንጅት የተገኘ የልማት ድል ነው ያሉት አምባሳደሯ፤ ይህም መዲናዋን የአፍሪካ የአመራርና የልማት ጥበብ የሚቀሰምባት የስልጣኔ ተምሳሌት አድርጓታል ብለዋል።

በኢትዮጵያዊያን ጠንካራ የሥራ ባህል የተገኘው አስደናቂና ፈጣን የመሰረተ ልማት ዕድገትም የአመራርና የልማት ክፍተት ለሚፈትናቸው የአፍሪካ ከተሞች ትልቅ ትምህርት እንደሚያስተላልፍ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም