በ"ምርጫዬ" መተግበሪያ አማካኝነት ባለንበት ሆነን የመራጭነት ካርድ መውሰዳችን ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም አስችሎናል - ኢዜአ አማርኛ
በ"ምርጫዬ" መተግበሪያ አማካኝነት ባለንበት ሆነን የመራጭነት ካርድ መውሰዳችን ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም አስችሎናል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በ"ምርጫዬ" መተግበሪያ አማካኝነት ባሉበት ሆነው የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸው ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማስቻሉን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካርዳችንን በመጠቀም የተሻለ ሃሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ነዋሪዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ለአንድ ወር እንደሚቆይ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ ዜጎች በምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ወይም "ምርጫዬ" የተሰኘውን መተግበሪያ በስልካቸው በመጫን መመዝገብ እንደሚችሉ ማሳወቁ ይታወቃል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች የዲጂታል ምዝገባ አማራጭ መፈጠሩ ያለምንም እንግልትና ወረፋ ባሉበት ቦታ ሆነው የመራጭነት ካርዳቸውን እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ አብነት ንጉሴ፤ ምርጫ የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መምረጥ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ምዝገባ በዲጂታል መንገድ በቀላሉ መውሰዳቸውን ጠቅሰው በካርዳቸው ለሀገር ዕድገትና ልማት ይበጃል የሚሉትን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ሰላም በላይነህ በበኩላቸው፤ በምርጫው ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ ዜጋ ሁሉ የመራጭነት ካርድ በማውጣት መሳተፍ እንዳለበት ገልጸዋል።
የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ በሁለት መንገድ መመዝገብ መቻሉ ሂደቱን ቀልጣፋ ማድረጉን ጠቁመው፤ ያለምንም እንግልት ባሉበት ቦታ ሆነው "ምርጫዬ" መተግበሪያን በመጠቀም የመራጭነት ካርድ መውሰድ መቻላቸውን ተናግረዋል።
ምርጫው የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ የመራጭነት ካርድ መውሰድ እንዳለበት የገለጹት ደግሞ አቶ ደረጄ ማሞ ናቸው።
ዓለም በቴክኖሎጂ እየዘመነ ባለበት ወቅት አሰራሮችን ለማዘመን የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፤ የዘንድሮው ምዝገባ በኦንላይን መከናወኑ ጊዜን ከመቆጠብ ባለፈ የምዝገባ ወረፋን እንዳስቀረላቸው አብራርተዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ መስፈርቱን የሚያሟሉ ዜጎች ሁሉ በ"ምርጫዬ" መተግበሪያ አሊያም በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት በወቅቱ እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 10 ሺህ 934 ዕጩዎች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያመላክታል።
ከእነዚህም ውስጥ 2ሺህ 198 ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም 8 ሺህ 736 ዕጩዎች ለክልል ምክር ቤቶች መመዝገባቸው ተጠቁሟል፡፡