ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ትክክለኛ መረጃ ይዞ በንቃት እንዲሳተፍ የበኩላችንን እንወጣለን-የኮሙኒኬሽን የሥራ ሃላፊዎች

ሰቆጣ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ይዞ በንቃት እንዲሳተፍ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ሥራ ሃላፊዎች ገለፁ።

በ"ምርጫዬ" መተግበሪያ አማካኝነት ባለንበት ሆነን የመራጭነት ካርድ መውሰዳችን ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም አስችሎናል

በአንድ ሀገር ዴሞክራሲያዊ ሥርአት እንዲጠናከር ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ምርጫ ሲሆን ዜጎች የሚመራቸውን ፓርቲ በነፃነት መምረጥ የሚያስችላቸው ሥርአት ነው።

በኢትዮጵያም 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫን በመጪው ግንቦት ወር ለማከናወን የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል።

በምርጫ ወቅት ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት መራጩን ህዝብ ለማደናገር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ተቋማት ስላሉ ይህንን ለመከላከል ለመራጩ ህዝብ ትክክለኛ መረጃ ማድረስ ያስፈልጋል። 

ህዝቡ ይሆነኛል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችለውን መረጃ በትክክልና በወቅቱ በማድረስ ሀሰተኛ መረጃን በመከላከል በኩል ደግሞ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ኢዜአ ያነጋገራቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን የሥራ ሃላፊዎች እንዳሉት፤ የህብረተሰቡን ሰላም፣ አንድነትና የልማት ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል።  

በተለይ አሁን በምርጫ ወቅት ሃሰተኛ መረጃዎችን በመመከት ህዝቡ ትክክለኛና ተጨባጭ መረጃዎችን እንዲያገኝ እየሰሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት።


 

የብሔረሰብ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ እንዳሉት፤ በአስተዳደሩ ህብረ ብሔራዊነትንና የሃገር ሰላምና አንድነትን የሚያጠናክሩ የተግባቦት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

በተለይም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ በምርጫው ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ምርጫው ነጻ፣ አሳታፊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት መራጩን ህዝብ ለማደናገር የሚደረግ ጥረትን በመመከት ተጨባጭ መረጃን ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ማህበረሰቡ ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ሚዲያዎችን ለይቶ እንዲያውቅ ከማድረግ ባሻገር ከአርሶ አደሩ ጋር ገጽ ለገጽ ውይይት በማድረግና በተለያዩ አማራጮች ሃሰተኛ መረጃዎች የማጋለጥ ስራ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

ሃሰተኛና አሳሳች መረጃዎችን በመመከት ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ እያደረሱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰለሞን መዓዛ ናቸው።


 

የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ሁሌም የመረጃዎች ትክክለኛነትን በአግባቡ መመርመር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የህዝብን አንድነትና ሰላም የሚያደፈርሱ መረጃዎችን ከመመከት ባለፈ ሕብረ ብሔራዊነትን የሚያጠናክሩ የተግባቦት ሥራዎች እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ፓርቲ በነጻነት መምረጥ እንዲችል ስለምርጫው ሂደት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲይዝ በማድረግ በኩል የተጀመረው ሥራ እንደሚጠናከርም ጠቁመዋል።

የጋዝጊብላ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ማሞ በበኩላቸው፤ ለህዝብ ተጨባጭና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

ምርጫን በማስመልከት ዜጎች ማወቅ ያለባቸውን መረጃዎች በትክክለኛ መንገድ በማድረስ ህብረተሰቡ ስለምርጫው በቂ እውቀት ይዞ በንቃት እንዲሳተፍ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሑሴን (ዶ/ር) በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሚገኙ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት የምርጫ ሂደቱን ለማወክ የሚሰራጩ አፍራሽና አሳሳች መረጃዎችን በአግባቡ መመከት እንደሚገባ ማስገንዘባቸው የሚታወቅ ነው።

በተለይም ለህዝብ የጠራና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ በማድረግ ግልፅነትን ከመፍጠር ባለፈ ለምርጫው ስኬታማነት በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም