ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ  እየተደረገ ነው

ጎንደር ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን ለመጪው የመኸር ወቅት እርሻ ከሚያስፈልገው ማዳበሪያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ዞኑ ደርሷል

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የግብርናውን ምርታማነት በዘላቂነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በዚህም ለ2018/19 የምርት ዘመን 623 ሺህ ኩንታል ዘመናዊ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ታቅዶ በተደረገ ጥረት እስካሁን ከ240 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነውን ወደ ዞኑ በማስገባት ወደ ወረዳዎች እየተሰራጨ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 


 

በገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል በ15 ወረዳዎች እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመው ቀሪውን እስከ መጪው ሚያዚያ ወር ድረስ ሙሉ በሙሉ በማስገባት ለማሰራጨት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የስርጭቱን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥም ግብረ ሃይል በማቋቋም እያንዳንዱ አርሶ አደር ባለው የመሬት ልኬት መጠን እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑ ተናግረዋል። 

ከዚህ በተጨማሪም ለምርት ዘመኑ ጥቅም ላይ የሚውል 52 ሺህ ኩንታል የበቆሎ፣ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የቢራ ገብስና የአኩሪ አተር ምርጥ ዘር በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የምንዝሮ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ማዘንጊያ ጣሰው እንደገለጹት፤ ደጋግመው በማረስ ለዘር እያዘጋጁት ለሚገኘው መሬት አራት ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።


 

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በ2018/19 ምርት ዘመን ከ620 ሺህ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬትን በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ19 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም