ቀጥታ፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ሀገር በቀል ክህሎትን በማጎልበት የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ሀገር በቀል ክህሎትን በማጎልበት የዜጎችን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ገለጸ። 

የተቀናጀ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የዜጎች ተጠቃሚነት ማጎልበቻ ሆነዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዜጎችን የዲጂታል ፈጠራና ክህሎት ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው። 

በተለይም በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ሳይበር ደኅንነት ያሉ አዳዲስ የሥልጠና መርሃ ግብሮች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

ለዚህም የክህሎት ማበልጸጊያ ቴክኖሎጂዎችን በማሟላት የግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና መሰል ዘርፎችን ምርታማነት የሚያሻሽል ሀገር በቀል የፈጠራ ክህሎት እንዲጎለብት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት መሳለጥ መሰረት መጣሉንም ዋና ዳይሬክተሩ አውስተዋል።

የ2030ው ስትራቴጂ ደግሞ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ሥርዓቱን የበለጠ በማዘመን ረገድ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ሀገር በቀል የፈጠራ ክህሎትን በማጠናከር ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ምርምር ውጤቶችን እንዲያፈልቁ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም የሰልጣኞችን የቅበላ አቅም በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ወጣት ስራ ፈጣሪዎችም ስትራቴጂውና የተሰጣቸው ስልጠና ለስኬታቸው መነሻ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቴክኒክና ሙያ የኢንጂነሪንግ ምሩቅና የዜድ.ቲ.አይ አግሮ ቴክኖሎጂ (ZTI Agro-Technology) መስራች ወጣት ዘላለም እንዳለው፤ የኢትዮጵያ ዲጂታል ስትራቴጂ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ክህሎታቸውን እያሳደገላቸው መሆኑን ተናግሯል።


 

የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን አምራች አቤል ከበደ በበኩሉ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተተገበረው "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የፈጠራ ክህሎትን በማጎልበት በተኪ ምርትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጿል።


 

የቴክኒክና ሙያ የክህሎት ስልጠና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ወጪ ቆጣቢ የግብርና ማቀነባበሪያ ማሽኖችን ለማምረት እንዳስቻላቸው የገለጸችው ደግሞ ኢልሃም አሊ ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም