ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ፣ የወንዝ ዳርቻ፣ የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት ስኬቶች ጤናማ የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር መፍጠር አስችለዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 30 /2018(ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ፣ የወንዝ ዳርቻ፣ የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት ስኬቶች ጤናማ የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር መፍጠር ማስቻላቸውን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ተምሳሌታዊ ተግባር ነው

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ በሁለተኛው ዙር ፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ በአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ ፈጠራና የሕግ ተከባሪነት ስኬታማ ስራ ተሰርቷል።

የአረንጓዴ አሻራ፣ የወንዝ ዳርቻ፣ የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት ስኬቶችም የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ለፅዱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የፕላስቲክ፣ የአፈር፣ የውሃ፣ የአየርና የድምፅ ብክለትን በመከላከል የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል።

በንቅናቄው መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ15 ሚሊየን በላይ ከሚሆን ህዝብ ጋር የገፅ ለገፅ መድረክ በመፍጠር የአካባቢ ጥበቃና ፅዱ አካባቢ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን አንስተዋል።

በመገናኛ ብዙሃንም ከ50 ሚሊየን በላይ ህዝብ ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡ በአካባቢ ላይ የሚደርስ ብክለትን መቀነስ የሚያስችል የዕውቀት፤ የግንዛቤና የሕግ ማስከበር ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል።

በዚህም በሁለት ዙር የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የዜጎችን የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ በማሳደግ ፅዱና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል መሰረት መጣሉን ጠቅሰዋል።    

በቀጣይም 3ኛ ዙር የፅዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በ3ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ንቅናቄም የለውጡን ዓመታትን የአረንጓዴ አሻራ፣ የወንዝ ዳርቻ፣ የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት ስኬቶች በማጽናት ባህል ይሰራል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተተገበሩ የአረንጓዴ አሻራ፣ የወንዝ ዳርቻ፣ የገጠርና ከተማ ኮሪደር ልማት ስኬቶች የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ለፅዱ ኢትዮጵያ ግንባታ ወሳኝ ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማት ስራ የፍሳሽ አወጋገድና የቆሻሻ አያያዝን በማዘመን ዜጎችን ፅዱ የመኖሪያ ምኅዳር በማጎናጸፍ የወንዞችን ጤናማነት የሚያስጠብቅ ተምሳሌታዊ የልማት ስኬት መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃና የእርከን ሥራ የሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን በማስጠበቅ ገንቢ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታም ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሰሩ የግሉን ዘርፍ ማበረታታት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም