የተቀናጀ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የዜጎች ተጠቃሚነት ማጎልበቻ ሆነዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የተቀናጀ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የዜጎች ተጠቃሚነት ማጎልበቻ ሆነዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2018 (ኢዜአ)፡- የተቀናጀ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የመንግሥት አገልግሎት አፈፃፀም ቁልፍ የክዋኔ ማመላከቻ እና የዜጎች ተጠቃሚነት ማጎልበቻ ሆነዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሐረር ከተማ የተቋቋመውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጎብኝተዋል።
ከጉብኝታቸው በኋላም በሐረር ከተማ የተቋቋመው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል አቀናጅቶ የማቅረብ ሀገር አቀፍ መርሐ-ግብር አካል መሆኑን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ገልጸዋል።
አክለውም በሐረር የመሶብ ማዕከል 8 ተቋማት በ24 የአገልግሎት መስኮቶች 67 የተለያዩ የሕዝብ አገልግሎቶችን በአንድ ስፍራ ለተገልጋይ ያቀርባል ብለዋል።
ይኸው ሀገራዊ አፈፃፀም የመንግሥት አገልግሎትን ብቃት፣ ተደራሽነት እና የዜጎች እርካታ በማሻሻል፣ በተቋማት መካከል የተበታተነ አገልግሎትን በመቀነስ፣ ኅብረተሰቡ አገልግሎት ለማግኘት የሚያጠፋውን ጊዜ እና ገንዘብ መቀነስ አስችሏልም ነው ያሉት።
በመላው ሀገራችን የመሶብ ሥነ-ዘዴ፤ መንግሥት ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የተቀናጀ የአገልግሎት አሰጣጥ ያለውን ጽኑ ዐቋም በሚያመላክት መንገድ እየተስፋፋ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የተቀናጀ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የመንግሥት አገልግሎት አፈፃፀም ቁልፍ የክዋኔ ማመላከቻ እና አጠቃላይ የዜጎች ተጠቃሚነት ማጎልበቻ መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።