መገናኛ ብዙኃን የወል ትርክትን በመገንባት ብሔራዊ ጥቅምን ሊያስጠብቁ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን የወል ትርክትን በመገንባት ብሔራዊ ጥቅምን ሊያስጠብቁ ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ) ፦ መገናኛ ብዙኃን የወል ትርክትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት ብሔራዊ ጥቅምን ሊያስጠብቁ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና የልዕልና ጉዞዋን ለዓለም ማስተዋወቅ የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ተግባር ሊሆን ይገባል
የሀገር ግንባታና ብሔራዊ ጥቅም ከፖለቲካ በላይ መሆኑንም ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን "መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፥ የመደመር መንግሥት ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማረጋገጥና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ስትራቴጂካዊ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የጋራ እሴቶችን በማጎልበትና ጠንካራ የወል ትርክትን በመገንባት ኅብረ ብሔራዊ እንድነትን ያጠናከሩና ለሀገራዊ ብልጽግና መሠረት የሆኑ ተግባራት መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
መገናኛ ብዙኃን ለሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አማካሪ ሚኒስትሩ ትኩረታቸውን ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከርና ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ላይ ማድረግ እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያን የማበልፀግ ራዕይ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ድርሻ መሆኑን ጠቅሰው ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ለመገንባት ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አክለውም ያለ አንዳች ልዩነት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ሉዓላዊነትን ማስከበር ከሁሉም ዜጋ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሃይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኃን ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግሥት ባከናወናቸው ዘርፈ-ብዙ ሪፎርሞች የመገናኛ ብዙኃን ምህዳሩ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰፋ መደረጉን ተናግረዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የተሰማሩ አካላት እውነተኛ መረጃን ለህዝብ በማድረስ ረገድ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።