ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና የልዕልና ጉዞዋን ለዓለም ማስተዋወቅ የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ተግባር ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና የልዕልና ጉዞዋን ለዓለም ማስተዋወቅ የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ 

መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል - ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን "መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው አገር አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም፣ ፍላጎትና እያደገ የመጣውን አቅም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚያስተዋውቅ መልኩ አጀንዳዎቻቸውን ሊቀርጹ ይገባል፡፡ 

ብሔራዊ ጥቅምን ማስተዋወቅ ማለት ኢትዮጵያ ለመለወጥ፣ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥና በዓለም መድረክ ተገቢ ስፍራዋን ለመያዝ ያላትን ጽኑ ፍላጎት ማሳየት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል መገናኛ ብዙኃን በአደረጃጀት፣ በይዘት ጥራትና በሰው ኃይል አቅም ራሳቸውን በማዘመን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ብሔራዊ ጥቅም ሲከበር የሀገርና የሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሚዲያ ተቋማትም ጥቅም ይጠበቃል፡፡ 


 

በመሆኑም የሚዲያ አመራሮችና ባለሙያዎች ለዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ አንደሞ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ይበልጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። 


 

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ መረጃ ሰጪዎችም ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እንደገለጹት፤ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስረጽ ከመደበኛው የዜና አቀራረብ ባለፈ የመዝናኛ ዘርፉን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው። 


 

እንደ ሆሊውድ ያሉ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመጥቀስ የታቀደበትና ግልጽ ዓላማ ያለው የጥበብ ሥራ ሕዝብን እያዝናና ቁምነገር ማስተላለፍ እንደሚችል አስገንዝበዋል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነትና የዲፕሎማሲ ስኬት ለማሳደግ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ ልዩ ዕውቀት ያላቸው ጋዜጠኞች ሚና የማይተካ ነው ብለዋል። 


 

ወቅታዊ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሁኔታዎችን በሚገባ የተረዱና አጀንዳ ተኮር የሆኑ የሚዲያ ባለሙያዎችን ማፍራት፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ትክክለኛውን መረጃ ለዓለም ለማድረስ ዋነኛው ስትራቴጂካዊ መሣሪያ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በሰጡት ማጠቃለያ፤ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ህልውናን፣ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናን እና ማህበራዊ አንድነትና ሌሎችን ጉዳዮች የማሳካት ስትራቴጂካዊ ግብ ነው ብለዋል። 


 

በዚህም መገናኛ ብዙኃን እያከናወኑት ያለው ሥራ አበረታች እንደሆነና ይህን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም