በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በተቀናጀ ሁኔታ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በተቀናጀ ሁኔታ እየተከናወነ ነው
አርባ ምንጭ ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦በጋሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ተግባር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በተቀናጀ ሁኔታ እየተሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
እየጣለ ያለው ከፍተኛ ዝናብ በጋሞ ዞን በጋጮ ባባ እና በቦንኬ ወረዳዎች እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያ ወረዳ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋን አስከትሏል።
በክልሉ በበልግ ወቅት እየጣለ ባለው ዝናብ ጎርፍን ጨምሮ የመሬት መንሸራተት አደጋ እያጋጠመ በመሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ኮሚሽኑ አሳሰበ
አደጋውን በተመለከተም የአገልግሎቱ ኃላፊ አቶ ሃይለማሪያም ተስፋዬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በአደጋው ሳቢያ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በተቀናጀ ሁኔታ እየተሰራ ይገኛል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በከተማዋ የሚገኘው የኩልፎ ወንዝና በዙሪያ ወረዳ የሰጎ ወንዝ ሙላት አርባ ምንጭ ከተማን ጨምሮ በአራት ወረዳዎች የተከሰተው አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋን አስከትሏል።
እንዲሁም አደጋው በኢንተርፕራይዞች፣ በትምህርት ቤቶችና በሌሎች ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ የክልሉ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ዕርዳታና መልሶ ማቋቋም ለማከናወንም የአደጋ ጊዜ ማዕከል ተቋቁሞ ስራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።
ከሀብት ማሰባሰብ ስራ ጋር በተያያዘ የዓይነት ድጋፍ የሚያቀርቡ አካላትና ድርጅቶች ከጋሞ ዞን አስተዳደር ጋር በመገናኘት ድጋፍ እንዲደረግ በጋሞ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት በሒሳብ ቁጥር 1000321312865 በኩል ገቢ ማድረግ እንደሚቻል አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ባወጣው የአየር ትንበያ መረጃ መሠረት የዝናቡ ሁኔታ ለ10 ቀናት የሚቀጥል በመሆኑ ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሰዎች ተዳፋታማ፣ የጎርፍ መውረጃና የመሬት መሰንጠቅ ምልክት ከሚታይባቸው አካባቢዎች መራቅ እንዳለባቸው አመልክተው ህፃናትን ጨምሮ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ኃላፊው አሳስበዋል።