ቀጥታ፡

በክልሉ በበልግ ወቅት እየጣለ ባለው ዝናብ ጎርፍን ጨምሮ የመሬት መንሸራተት አደጋ እያጋጠመ በመሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ኮሚሽኑ አሳሰበ

አርባምንጭ ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበልግ ወቅትን ተከትሎ እየጣለ ባለው ዝናብ ጎርፍን ጨምሮ የመሬት መንሸራተት አደጋ እያጋጠመ በመሆኑ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራርና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን አሳሰበ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራርና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ወገኔ ብዙነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የበልግ ወቅትን ተከትሎ እየጣለ ያለው ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ እያስከተለ ነው።


 

በክልሉ በጋሞ፣ በወላይታ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በኮንሶ፣ በጌዲኦ እና በጎፋ ዞኖች በሚገኙ ተራራማ አካባቢዎች ያልተጠበቀ የመሬት መንሸራተት እንዲሁም በአንዳንድ ቆላማ አካባቢዎች ደግሞ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል አመላክተዋል።

ስለሆነም ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የክልሉ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ህብረተሰቡ በየአካባቢው አጠራጣሪ የሆኑ የመሬት መሰንጠቆች፣ የውሃ ምንጮችና ሌሎች ለውጦች ሲከሰቱ በፍጥነት ለሚመለከተው ክፍል መረጃ በመስጠት ብሎም ስጋት ወደሌለባቸው አካባቢዎች በመሄድ ራሱን ከአደጋው እንዲጠብቅ አስገንዝበዋል።

ኮሚሽነር ወገኔ አክለውም በክልሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን በዘላቂነት ለመከላከልም በአረንጓዴ አሻራና የተፋሰስ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በክልሉ በተለያዩ ዞኖች በተፈጥሮ አደጋ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ስጋት ወደሌለባቸው አካባቢዎች በማስፈር መልሶ የማቋቋም ስራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰዋል።

ችግሩን በሳይንሳዊ መንገድ በዘላቂነት ለመከላከል በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።


 

የጋሞ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍና ማኑቆ በበኩላቸው፤ ትናንት ምሽት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ በዞኑ ቦንኬ እና ጋጮ ባባ ወረዳዎች በመሬት መንሸራተት አደጋ የሰው ህይወት ማለፉን ገልጸዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ እና ዙሪያ ወረዳ የኩልፎ እና የሴጎ ወንዞች ሙላት ባስከተሉት የጎርፍ አደጋ በተለያዩ ተቋማትና መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የአደጋው መጠን እየተጣራ መሆኑን ጠቁመው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ከነዋሪዎች፣ ከግብረ-ሰናይ ድርጅቶችና ከባለሀብቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም