ቀጥታ፡

ሴት አመራሮችና ምሁራን የማህበረሰቡን ችግር በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለሀገር ልማት መትጋት ይኖርባቸዋል

ሀዋሳ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ በየደረጃው ያሉ ሴት አመራሮችና ምሁራን የማህበረሰቡን ችግር በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በሀገር ግንባታ ሂደት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት መምህራን ትውልዱን በተሻለ መልኩ የሚቀርጹ ናቸው

"50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በውይይትና በመስክ ምልከታ ተከብሯል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፤ መንግስት የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባከናወናቸው ተግባራት ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ለእነዚህ ውጤቶች ቀጣይነትም የምሁራን ሚና የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን በሲዳማ ክልል ወንዶገነት ከተማ ባደረጉት ምልከታ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በኢንዱስትሪው ዘርፍም የሴቶች አሻራ ጎልቶ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ትውልድን የሚሻገር ሥራ በኃላፊነት በመሥራት የሴቶችን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 

በየደረጃው ያሉ ሴት አመራሮችና ምሁራን የማህበረሰቡን ችግር በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በሀገር ግንባታ ሂደት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ፍስሃ ጌታቸው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራ በተጨማሪ ሴቶችን የማሳተፍ የምርምርና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 


 

በተለይም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና እና በሕክምና ዘርፎች የሚመረቁ ሴት ተማሪዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሴት ተመራማሪዎችን በማደራጀት በሴቶች ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ በፆታ እኩልነትና ጥቃት መከላከል፣ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ እና በጤና ጉዳዮች ላይ ችግር ፈቺ ምርምሮች እንዲካሄዱ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው፤ በክልሉ ከ28 ሺህ በሚበልጡ የልማት ህብረቶች ሴቶችን በማደራጀት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎአቸውን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 


 

በግብርናው መስክ የተደራጁ ሴቶች አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ ጤናማ የአመጋገብና የአኗኗር ሥርዓትን በማሻሻል ሀብት ማፍራት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በወንዶገነት ወረዳ በልማት ህብረት ተደራጅተው ውጤታማ ከሆኑ ሴቶች መካከል ወይዘሮ ሙሉነሽ ሙላት አንዷ ሲሆኑ፤ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት በተመቻቸላቸው ቦታ ላይ በመኸር ጤፍ ካመረቱ በኋላ፣ በጓሮ አትክልት ልማት ተሰማርተው የግልና የማህበሩን ቁጠባ ማሳደጋቸውን ገልጸዋል፡፡ 


 

የልማት ህብረቱ ከገቢ ማሻሻያነት ባለፈ በጤና እና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ በር እንደከፈተላቸውም ተናግረዋል፡፡

በመርሐግብሩ  በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና በወንዶገነት ወረዳ የመስክ ምልከታ የተደረገ ሲሆን፤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት  አመራሮች፣ ምሁራንና ሴት ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም