በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት መምህራን ትውልዱን በተሻለ መልኩ የሚቀርጹ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሴት መምህራን ትውልዱን በተሻለ መልኩ የሚቀርጹ ናቸው
መቱ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ሴት መምህራን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ከማስተማር ስራቸው ባሻገር ትውልዱን በተሻለ መልኩ በመቅረጽ ረገድ አርአያነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡
ሴቶች በሁሉም ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጠናከር ይገባቸዋል
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን "50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ'' በሚል መሪ ሀሳብ በመቱ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል።
በመድረኩ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ እንደገለጹት፤ በለውጡ ዓመታት መንግሥት ለሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሴቶች ያሉባቸውን ባህላዊና ውጫዊ ተጽዕኖዎች በመቋቋም እየተፈጠሩ ያሉ እድሎችን በአግባቡ ሊጠቀሙ ይገባል ነው ያሉት።
በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ሴት ምሁራን በትውልድ ግንባታ ላይ ያላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት በፈጠራ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በቴክኖሎጂ አቅማቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዓለሙ ዲሳሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚከናወኑት ተግባራት ለቤተሰብና ለሀገር ብልጽግና መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።
ሴቶች ከቤተሰብ ጀምሮ ለአመራርነት የቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሚሰነዘሩባቸውን የአመለካከትና የባህል ተጽዕኖዎችን አሸንፎ ለመውጣት የተሻለ ጥረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኢሉአባቦር ዞን አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ምትኬ ለገሰ በበኩላቸው፤ መንግሥት የሴቶችን የኢኮኖሚ፣ የአመራርነትና የቴክኖሎጂ አቅም ለማጎልበት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ የሆኑት መምህርት ትዕግስት ተክሉ እና መምህርት እምነት ደበላ፤ ሴት መምህራን ከመምህርነት ባለፈ ያላቸውን እውቀትና ልምድ በማጠናከር በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሚናቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሴቶች ያሉባቸውን ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ከግምት ውስጥ በማስገባትም ተጨማሪ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሕብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ አሚራ ፋቲ በበኩሏ፤ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪነት በማምጣት ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው ስትል ገልጻለች።
በዕለቱም በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀና የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን ነባራዊ ሁኔታ፣ አስተዋጽኦ፣ የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎችና በሀገር ግንባታ ያላቸውን ሚና የሚዳስስ የውይይት ሰነድ ቀርቧል።