በምክክር የሚገነባ ብሔራዊ መግባባት ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ብልፅግና መሳካት ወሳኝ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
በምክክር የሚገነባ ብሔራዊ መግባባት ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ብልፅግና መሳካት ወሳኝ ሚና አለው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የጀመረችው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠርና ሥር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት ለዘላቂ ሰላምና ለሀገር ብልፅግና መሳካት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ምሁራን ገለጹ።
ሀገራዊ ለውጡ ለዳበረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል
ሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን፣ የሙያ ማህበራትንና የፖለቲካ ኃይሎችን በንቃት በማሳተፍ፣ ለዘመናት የቆዩ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የተለያዩ ምሁራን እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ምክክር የዜጎችን የጋራ ፍላጎት በማንፀባረቅ ለሀገራዊ አንድነትና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ተመራማሪ ማናየ ዘገየ (ዶ/ር)፤ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ውስብስብ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በየትኛውም ሀገር የሐሳብ ልዩነት መኖሩ የማይቀር መሆኑን የጠቆሙት ምሁሩ፣ ዋናው ቁምነገር እነዚህን ልዩነቶች በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ማስተናገድ መቻሉ ላይ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም በልዩነቶች ዙሪያ ለመወያየት የሚያስችል ጠንካራ የምክክር ሥርዓት መዘርጋት ለሀገር ግንባታና ለብሔራዊ መግባባት ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ ሂደት የሐሳብ ልዩነቶችን ወደ ዕድል በመቀየር ለሀገራዊ አንድነትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ መሠረት ይጥላል ብለዋል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ገመቺስ መርሻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ሀገራዊ ምክክሩ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ተነጋግሮ እልባት ለመስጠት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ሂደቱ ያለፉ በደሎች በይቅርታ የሚታረሙበትና ፍትሕ የሚረጋገጥበት ወሳኝ መድረክ መሆኑንም አንስተዋል።
በበርካታ ችግሮች ውስጥ የነበሩ አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት በዚህ የምክክር ሂደት አማካይነት ወደ መግባባት መምጣታቸውን እንደ መልካም ተሞክሮ በመጥቀስ፥ ሂደቱ ለሀገራዊ መግባባት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችው የምክክር ሂደት የሀገርን ዕጣ ፈንታ በጥቂት ልሂቃን እሳቤ ብቻ ከመወሰን ይልቅ፣ በሁሉም ዜጎች ተሳትፎና ፍላጎት ላይ እንዲመሰረት እንደሚያደርግም አክለዋል።
ምሁራኑ አያይዘውም፣ ሀገራዊ ምክክሩ ሥር የሰደዱ የፖለቲካና የማህበራዊ ችግሮችን በመለየት፣ ጠንካራና ገዢ የሆነ ብሔራዊ ትርክት ለመገንባት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
ይህ ግብ ሊሳካ የሚችለው ለነገው ትውልድ የሚተርፍ አርቆ አሳቢነትና በልዩነቶች ላይ በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር መሆኑን አስገንዝበዋል።
መመካከር ትርፍ እንጂ ኪሳራ እንደሌለው የገለጹት ምሁራኑ፣ በዚህም የሚገኘው የጋራ መግባባት ለሀገሪቱ ውስጣዊ አንድነት፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለተቀላጠፈ ልማትና ለዘላቂ ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።