ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡ ለዳበረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ ጤናማ የፖለቲካ ምኅዳር በመፍጠር ለዳበረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል ሲሉ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።

ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማግስት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመንግስታዊ የኃላፊነት ቦታ ተመድበው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን የሚያገለግሎበት ዕድል መፈጠሩንም ተናግረዋል።

የፓርቲው ሊቀመንበር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ለውጡ ለመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ፉክክር ምቹ ምኅዳር ፈጥሯል።

የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት በምርጫ ወቅት አብላጫ ድምፅ ባያገኙም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን የሚያገለግሉበት ታሪካዊ የፖለቲካ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

የፓርቲያቸው አመራር አባላትም በአስፈፃሚ አካላት ውስጥ በአመራርነት በመስራት በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አሻራ እያሳረፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር የሚሰሩበት ዕድል መፈጠሩ የዴሞክራሲ ባህልን በማጎልበት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ይህም በፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ልዩነት ሚዛን በማስጠበቅ ውስጥ የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

ከለውጡ በፊት ፖለቲካ ፓርቲዎች ይገጥማቸው የነበረ የምኅዳር መጥበብ ጤናማ የፖለቲካ ምኅዳርን በማወክ ከትብብር ይልቅ ጥርጣሬ የተሞላበት ግንኙነት እንዲፈጠር አድርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ላይ የሚኖራቸውን ገንቢ አበርክቶ በማሳጣት አሻራቸውን እንዳያሳርፉ በማድረግ ሳንካ ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጥ አማራጭና ብዝኅ እሳቤን በማጎልበት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት መስፈን አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።

የቀድሞው ኋላቀር የፖለቲካ ባህልና ሥርዓት ሃሳብን በሃይል ለማስፈፀም የተሄደበት ርቀት ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ ሲያስከፍላት እንደቆየ አብራርተዋል።

በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የተፈጠረው አስቻይ የፖለቲካ ምኅዳር ዜጎች በአቅማቸው ልክ ሀገራቸውን የሚያገለግሎበት ዕድል እንደፈጠረም ነው የተናገሩት።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) አመራር አባላት የተሰጣቸውን ዕድል በመጠቀም በፌደራልና በክልል የመንግስት መዋቅር የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግስት አስደናቂና አዲስ የፖለቲካ ባህል ፈጥሯል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ አሁን የተጀመረው ብዝኅነትን የሚያስተናግድ የሃሳብ ገበያና የፖለቲካ ፉክክር ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም