ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል - ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትር የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን "መገናኛ ብዙኃን ለብሔራዊ ጥቅም" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

የጠቅላይ ሚኒስትር የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል።

የመደመር መንግስት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የወል ትርክት በመገንባት የህዝብ የጋራ እሴቶችን በማጎልበትና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።


 

መገናኛ ብዙኃን ለሀገር ግንባታ ትልቅ አበርክቶ ያላቸው መሆኑን ጠቁመው በዚሁ መሰረት የሀገርንና የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን የማበልጸግ እሳቤ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ድርሻ መሆኑን ገልጸው ለኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ለሀገር ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅና ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት በኩል መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግስት ባደረገው ሪፎርም የመገናኛ ብዙሃን ምህዳር መስፋቱን ተናግረዋል።

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰማሩ አካላት እውነተኛ መረጃን ለህዝብ በማድረስ በኩል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም