በበልግ ዝናብ ተጠቃሚና ሰብል አብቃይ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ለግብርና ስራ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በበልግ ዝናብ ተጠቃሚና ሰብል አብቃይ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ለግብርና ስራ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ በቀጣዮቹ አስር ቀናት በበልግ ዝናብ ተጠቃሚና ሰብል አብቃይ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ለግብርና ስራ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለፀ።
ኢንስቲትዩቱ ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 11 ቀን 2018 ዓ.ም የሚኖረውን የአየር ሁኔታ አዝማሚ አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በቀጣዮቹ አስር ቀናት ለዝናብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገፅታዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
ኢትዮጵያ የሰርኩላር ኢኮኖሚን የልማት እቅዷ አካል በማድረግ በአካባቢ ጥበቃ ለአፍሪካ አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች ትገኛለች
በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በደቡብ እና በደቡብ ምስራቅ፣ የስምጥ ሸለቆና አጎራባች አካባቢዎች፣ የመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ላይ የተሻለ ገፅታ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
በዚህም በደቡብ፣ መካከለኛው፣ ምስራቅና እና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
እነዚህ አካባቢዎች በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በዚህም መሰረት ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴዮ፣ ጋሞ፣ ባስኬቶ፣ አሪ፣ ኮንሶ፣ ቡርጂ፣ አሌ፣ ጋርዱላ፣ ኮሬ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም ሁሉም የሲዳማ ክልል ዞኖች ከመካከለኛ እስከ ከባድ የዝናብ መጠን ያገኛሉ ብሏል ኢንስቲትዩቱ።
ይህ የዝናብ መጠን በቂ የአፈር እርጥበት እንዲኖር፣ የሰብሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት፣ ለቋሚ ተክሎች እድገትና የግጦሽ ሳርና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል እንዲኖር በማድረግ ለግብርና ሥራ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ጠቅሷል።
የአፈር መሸርሸር፣ በሰብል ማሳ ላይ ውሃ መተኛት፣ የሰብል በሽታና ተባይ እንዲሁም የአረም መከሰት ሊያስከትል እንደሚችልም አስጠንቅቋል።
ስለሆነም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን መስራት፣ የሰብል በሽታንና አረም እንዳይስፋፋ መከላከል፣ የሰብል ማሳዎችን በቅርበት መከታተልና የአየር ጠባይ ትንበያና ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
በመሆኑም የአየር ሁኔታው አስተዋፅኦ በላቀ ሁኔታ ለመጠቀምና ሊከሰት የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦችን ከወዲሁ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስረድቷል።
በሌላ በኩል በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል-ጉሙዝና በምዕራብ አማራ አካባቢዎች ቀን ላይ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እንዲሁም ሌሊት ላይ ወበቅ እንደሚጠበቅ ገልጿል።