ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሰርኩላር ኢኮኖሚን የልማት እቅዷ አካል በማድረግ በአካባቢ ጥበቃ ለአፍሪካ አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች ትገኛለች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የሰርኩላር ኢኮኖሚን በሀገራዊ የልማት እቅዷ ውስጥ በማካተት በአካባቢ ጥበቃ ረገድ ለአፍሪካ አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኗን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ (ዶ/ር) ገለፁ።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከህንድ የሳይንስና አካባቢ ማዕከል ጋር በመተባበር ያዘጋጁት በሰርኩላር ኢኮኖሚ ላይ የሚያተኩረው 8ኛው የከተሞች ፎረም ከመጋቢት 1 እስከ 3 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

የአረንጓዴ አሻራ፣ የወንዝ ዳርቻ፣ የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት ስኬቶች ጤናማ የአካባቢ ሥነ-ምኅዳር መፍጠር አስችለዋል

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ (ዶ/ር) በፎረሙ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፣ የሰርኩላር ኢኮኖሚ መርህ የአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እና የ10 ዓመቱ የልማት እቅድ አካል ነው። 

ስትራቴጂው የኢኮኖሚ እድገትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ማስተሳሰር፣ ዘላቂ የቆሻሻ አያያዝን እና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን ማጠናከር እንዲሁም በአረንጓዴ ስራ ፈጠራ በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ ያለመ ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም በግብርና፣ በምግብ ስርዓት እና በግንባታ ዘርፎች ላይ ያተኮረ ብሄራዊ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ-ካርታ ወደ ትግበራ መሸጋገሩን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለግል ዘርፉ ተሳትፎ ማዕከል የሚሆን "የሰርኩላር ኢኮኖሚ የልህቀት ማዕከል" በአዲስ አበባ የማቋቋም ሂደት መጀመሯን ገልጸዋል፡፡ 

ማዕከሉ የሀብት ምርታማነትን በማሳደግ እና በመላው አፍሪካ የአጋርነት ትስስርን በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል፡፡ 

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ደጀን በበኩላቸው በኢትዮጵያ የከተማ ልማት ስራዎች ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተሰናስለው እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።   


 

የሰርኩላር ኢኮኖሚ ከተሞች ሀብትን በብክነት ፈንታ ወደ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲቀይሩ የሚያስችል ማዕቀፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩመር ራይ በአፍሪካ እየታየ ላለው ፈጣን የከተሞች መስፋፋት ተስማሚ የአካባቢ ጥበቃ መፍትሄዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል። 


 

በዚህም ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማት እያከናወነች ያለው ተግባር ለሌሎች ሀገራት ትልቅ ትምህርት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የተከናወኑ የልማት ስራዎች ከተማን እንዴት መለወጥ እንደሚቻል በተግባር ማሳየት መቻሉን ጠቅሰው አዲስ አበባ አሁን ላይ ሰፋፊ መንገዶች፣ የብስክሌት መጓዣያዎች እና አረንጓዴ ስፍራዎች ያሏት ዘመናዊ ከተማ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም