ቀጥታ፡

ሴቶች በሁሉም ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጠናከር ይገባቸዋል 

ጅግጅጋ ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ ሴቶች በሁሉም ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጠናከር እንደሚገባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ተናገሩ።

የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን "50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ እንደገለጹት፤ ዛሬ የሚከበረው በዓል ሴቶች በሳይንስ፣ በምርምር በፖሊሲ ቀረጻና በቴክኖሎጂ እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት ያለመ ነው።

ሴቶች በሀገር ግንባታ ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ሴት ምሁራን ለሀገርና ለህዝብ ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።

በማህበረሰብ ውስጥ ሴቶች የህይወት መጽሐፍ መሆናቸውን አንስተው ስር የሰደዱ እና የሴቶችን ጉዞ የሚያደናቅፉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በእውቀት ለማስቆም ተግተው መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከሴት ምሁራን የሚጠበቁ ትላልቅ ሃላፊነቶች እንዳሉ አንስተው፣ ሃላፊነትን በውጤት የመወጣት ብቃትን ለወጣት ሴቶችና ተማሪዎች በተግባር ማስተማር እንዳለባቸውም እንዲሁ።

ሴት ምሁራን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በምርምር፣ በመማር ማስተማር ሥራና በተለያዩ ዘርፎች ብቃታቸውን በማሳየት ውጤታማ ከመሆን ጾታ እንደማይገድብ በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።

ሴት ምሁራን ለወጣት ሴቶች ብርሃንና ተስፋ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ምሁራኑ ስለ ሴቶች ያለውን የተዛባ አመለካከት በመቀየርና ፍትሃዊነት የሠፈነበት ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

ሴት ተማሪዎችን በማብቃት፣ በመምህርነት እና በምርምር እንዲሁም ህግ በመቅረጽ ረገድ የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።


 

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አማካሪ ወይዘሮ ፈሪሃ መሐመድ በበኩላቸው፤ ሴቶች በሁሉም ዘርፎች የሚያደርጉትን ተሳትፎ  እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ የሴት ምሁራን በሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረው ይህን ሚናቸውን አጠናክርው እንዲያስቀጥሉ አስገንዝበዋል።

የሶማሌ ክልል ሴቶች እና ህጻናት ጉዳዮች ምክትል ቢሮ ሃላፊ ኡባህ አብዱረህማን በበኩላቸው እንዳሉት፤ ሴቶች የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የማፍራት ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

የክልሉ ሴቶችም ይህንን ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በመድረኩ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በቀረበው ጽሁፍ ላይም ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም