ቀጥታ፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካርዳችንን በመጠቀም የተሻለ ሃሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ነዋሪዎች

ገንዳውኃ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦በቀጣይ ግንቦት ወር  በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካርዳችንን በመጠቀም የተሻለ ሃሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ሀገራዊ ለውጡ ለዳበረ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል 

በዞኑ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በመካሄድ ላይ ይገኛል። 

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ያየሽ አለሙ እንደገለፁት፤ በህገ-መንግስቱ ያገኙትን መብት በመጠቀም ለሀገርና ህዝብ ይበጃል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።


 

ምርጫ በህዝብ ድምፅ ስልጣን የሚያዝበትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገነባበት ሂደት መሆኑን በመገንዘብ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ማውጣታቸውን ገልፀዋል።

የአገራችንን ልማት ለማፋጠንና የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምርጫ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ለህዝብ ሰላም የቆመና ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና የሚያሻግር ፓርቲን ለመምረጥም በመገናኛ ብዙሃን የሚካሄዱ ክርክሮች በቂ እውቀት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።


 

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አበባ አያሌው በበኩላቸው፤ በምዝገባው ያደረጉትን የነቃ ተሳትፎ ተጠቅመው የተሻለ ሃሳብ ያለውን ፓርቲ በመምረጥ እንደሚደግሙት ገልፀዋል። 

ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከምርጫ ስነ-ስርዓት አስከባሪና ከፀጥታ አካላት ጎን ሆነው እንደሚሰሩም አብራርተዋል። 

"7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች የመጀመሪያዬ ተሳትፎ በመሆኑ ለእኔ ልዩ ያደርገዋል" ያለችው ደግሞ ወጣት ሰዓዳ ታደሰ ናት። 

ለወጣቶችና ሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የነገዋን ኢትዮጵያ የበለፀገች ያደርጋታል ብላ የምታስበውን ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ ማውጣቷን ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም