ቀጥታ፡

 የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን አስተዋፅኦ ሊያጠናክሩ ይገባል

አዳማ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ።

በአጽዋማቱ ወቅት የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህልን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል--የሃይማኖት አባቶች

በአዳማ ገልማ አባገዳ አዳራሽ "የመደመር መንግሥትና የእምነት ተቋማት" በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉን ሰላም እና ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል። 


 

በመድረኩ ላይ ከሁሉም ዞኖችና ከተሞች የተወጣጡ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አባቶችና መሪዎች እየተሳተፉ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ እንደገለጹት፣ የሃይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ እና በልማት ረገድ ያላቸው ድርሻ ትልቅ ነው።


 

የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ህዝቡን በማስተባበር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መረጋገጥ የላቀ ድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

ተቋማቱ ለሀገር ህልውናና ሉዓላዊነት መከበር አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰው አሁንም ትውልዱ በሥነ-ምግባርና በሀገር ፍቅር እንዲታነጽ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።

የሃይማኖት መሪዎችና ቤተ እምነቶች ሰላምን በማጽናትና ልማት እንዲፋጠን የሚጠበቅባቸውን መንፈሳዊና ማህበራዊ ኃላፊነት አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአዳማ ደብረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ካቴድራል አስተዳዳሪ መላከ ብርሃናት ቆሞስ አባ ማርቆስ ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት፤ "ሰላም ባለበት ቦታ ልማትና ወጥቶ መግባት አለ" ብለዋል። 


 

ቤተክርስቲያኗ ከመንፈሳዊ ተግባራት ጎን ለጎን ለሰላም ግንባታ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸው፣ ከእስልምናና ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር በመሆን በአብሮነትና በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል። 

የአዳማ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክትል ኃላፊ ሼህ ሁሴን አህመድ በበኩላቸው፤ "ሃይማኖት ሰላም ነው፤ ሰላም ደግሞ በሀገር ላይ ይጸናል" ብለዋል። 

የሃይማኖት አባቶች አስቀድመው የውስጥ ሰላም ሊኖራቸውና ለተከታዮቻቸውም ስለ ሰላም ሊሰብኩ እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነትና በፍቅር አብረው እንዲኖሩና መቻቻል እንዲሰፍን መስራት ከመንፈሳዊ መሪዎች የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

ሰላምን ለማነፅ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎቹ ተከታዮቻቸውን ጨምሮ ሰላምን ለሀገር መስበክ አለባቸውም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም