ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ለወጣቶች አዳዲስ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ነው

ጎንደር ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ለወጣቱ ትውልድ አዳዲስ የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እያስቻሉ መሆኑን የከተማዋ ወጣቶች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሀገርን ከታሪኳና መልክዓ ምድራዊ ጸጋዋ የማስታረቅ የህልውና ጉዳይ ነው

የጎንደር ከተማ አስተዳደር "ለሰላም ዘብ እንቆማለን፤ የልማት አርበኛ እንሆናለን" በሚል መሪ ሃሳብ ከወጣቶች ጋር በሰላምና ልማት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሂዷል። 

በመድረኩ ላይ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል አስቻለው በላይ እንደገለጸው፤ መንግስት የከተሞችን ልማትና እድገት ለማፋጠን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ አድርጓል።

ጎንደር ከተማም የኮሪደር፣ የፋሲል አብያተ መንግስት እድሳትና ሌሎች የልማት ሥራዎች ተቋዳሽ መሆኗን ተናግሯል።


 

ይህም ለከተማዋ የዳግም ትንሳኤ ብስራት ይዞ መምጣቱን ያነሳው ወጣቱ፣ በከተማዋ በተካሄዱ የልማት ሥራዎች ወጣቶችም በሥራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግሯል።

ወጣት ታምራት አምሳሉ በበኩሉ፤ በከተማው እየተከናወኑ ባሉ የልማት ፕሮጀክቶች ወጣቶችና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግሯል።

"ይሄን ተጠቃሚነታችንን ለማስቀጠል እኛ ወጣቶች በህብረትና በአንድነት በመሆን ሰላማችንን ለማስቀጠል በቁርጠኝነት መስራት አለብን" ያለው ወጣት ታምራት፣ ሰላምን የማይሹ አካላትን በመታገል የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብሏል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት መንበሩ ሽፈራው በበኩሉ እንዳለው፤ መንግስት የጀመራቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የወጣቱን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው።


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ታደሰ በመድረኩ እንደገለጹት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የወጣቱ የነቃ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው።

በልማት ፕሮጀክቶች ወጣቱ ያለውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ማረጋገጥ እንዲችል በአሁኑ ወቅት ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የክፍለ ከተሞች የወጣት አደረጃጀት መሪዎችና አባላት፣ የወጣትና ሴት ክንፍ አመራሮች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም