የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሀገርን ከታሪኳና መልክዓ ምድራዊ ጸጋዋ የማስታረቅ የህልውና ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሀገርን ከታሪኳና መልክዓ ምድራዊ ጸጋዋ የማስታረቅ የህልውና ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የንግድ ወደብ ፍለጋ ብቻ ሳይሆን ሀገርን ከታሪኳና መልክዓ ምድራዊ ጸጋዋ ጋር የማስታረቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ቀዳሚ የባሕር ኃይልና አስተማማኝ የብዝኅ የንግድ ወደቦች ባለቤት እንደነበረች በታሪክ ማኅደር የተሰነደ የአደባባይ ምስጢር ነው።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የፈጸሙት በደል ለጊዜውም ቢሆን ሀገርን ከስልጣኔ መነሻና ከተፈጥሮ ጸጋዋ እንድትርቅ በማድረግ የየብስ እስረኛ እንድትሆን ማድረግ ችለዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የተከናወኑ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ጥያቄውን በሚገባ በማስገንዘብ እንዴት ይፈጸም ወደሚል ስኬታማ ምዕራፍ ማሸጋገር ተችሏል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የንግድ ወደብ ፍለጋ ብቻ ሳይሆን ሀገርን ከታሪካዊ ማንነቷና መልክዓ-ምድራዊ ጸጋዋ ጋር የማስታረቅ የህልውና ጉዳይ ነው።
በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የታሪክ ተመራማሪ ዳግማዊ ተስፋዬ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የስልጣኔ ታሪክ ከቀይ ባሕር እና የባሕር በር ባለቤትነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ስትራቴጂካዊ የቀይ ባሕር ቅርበት የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገትን የማስቀጠል የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም ከ30 ዓመታት በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ የዕድገትና ስልጣኔ ታሪኮች ሁሉ ጠንካራ የባሕር ኃይልና አስተማማኝ የወደብ አገልግሎት ጋር ተሰናስለው የተሰነዱ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።
ከባሕር በር ባለቤትነት እንድትርቅ መደረጉ በንግድና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ የዕድገት ጉዞ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ ባሻገር መሰረታዊ ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ሌላኛው በዩኒቨርሲቲው የውሃ ምህንድስና ተመራማሪ ሲሳይ ደመቁ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሕጋዊ፣ ታሪካዊና አስተማማኝ የባሕር በር ባለቤት የነበረች ሀገር በተፈጸመባት በደል ከራሷ ወደቦችና የቀይ ባሕር ተጠቃሚነት እንድትርቅ መደረጉን አስታውሰዋል።
የዓለም አቀፍ የውሃ አካላት የጋራ ተጠቃሚነት መርህ፣ ታሪክ፣ ሕጋዊነትና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምክንያታዊ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ምሁራኑ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊ ስህተትን የማረምና ሀገርን ከተፈጥሮ ጸጋዎቿና ማንነቷ ጋር የማስታረቅ የህልውና ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለዚህም ታሪካዊና ሕጋዊ መሰረት ያለውን የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ጨምሮ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የቀጣናው ሀገራትም ለኢትዮጵያ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ አንስተዋል።