በአጽዋማቱ ወቅት የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህልን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል--የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በአጽዋማቱ ወቅት የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህልን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል--የሃይማኖት አባቶች
መቱ፤ አምቦ መጋቢት 3/2018 (ኢዜአ)፦ በአጽዋማቱ ወቅት የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት እና የአንድነት ባህልን የሚያጎለብቱ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ በኦሮሚያ ክልል መቱና አምቦ ከተሞች የሃይማኖት መሪዎችና ምእመናን ገለጹ።
ከሃይማኖት አባቶቹ መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኢሉአባቦር ሀገረ-ስብከት ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ታከለ ዳዲ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በዓብይ ፆም ወቅት ምእመናን ራሳቸውን ሳይሆን ሌሎች ወገኖቻቸውን በማስቀደም ፍቅርን፣ ርኅራኄንና ይቅርታን ሊያሳዩ ይገባል።
ይህ ተግባር ፈጣሪን የሚያስደስትና የሕዝቡን አንድነት የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጸዋል።
የመቱ ከተማ የነጃሺ መስጂድ ኢማም ሼህ ጣሂር ከሊል በበኩላቸው፤ የረመዳን ወር ሙስሊሙ ከመልካም ስራ ጋር ወደ ፈጣሪ የሚቀርብበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የተጣሉትን በማስታረቅ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና በመደጋገፍ እንዲሁም ለፍቅርና ለአንድነት ቅድሚያ በመስጠት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከመቱ ከተማ ምዕመናን መካከል አቶ በፈቃዱ ኦልጂራ እና አቶ አብዱ መሐመድ በበኩላቸው፤ ያለንን በማካፈል ከተቸገሩ ወገኖች ጋር ማሳለፍ በፈጣሪ ዘንድ ትልቅ ዋጋ ያለው ተግባር በመሆኑ፣ በፆም ወቅት ለሀገር ሰላምና ለሰው ልጆች ደህንነት በጋራ እንደሚጸልዩ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በአምቦ ከተማ የሚገኙ የእስልምናና የክርስትና እምነት አባቶችም፤ በረመዳንና በዓቢይ ጾም ወቅት ሕብረተሰቡ የተቸገሩ ወገኖችን ከመደገፍ ባለፈ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መስራት አለበት ብለዋል።
በአምቦ ከተማ የሚገኘው መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መላዕከ መንክራት ቆሞስ አባ ወልደ ማርያም መኩርያ ጾሙ የቂምና ጥላቻ መራቂያ፣ ይቅርታ የሚደረግበትና ለሀገር ሰላም የሚጸለይበት መሆኑን ገልጸዋል።
በዓቢይ ጾም ወቅት ሰላም የሚሰበክበትና መረዳዳት የሚጎላበት መሆኑን አብራርተዋል።
ሌላው የአምቦ ሃናን መስጂድ ዋና ኢማም ሼህ አልፊያ ከማል የረመዳን ወር የመደጋገፍ ወር መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የጎዳና ላይ አፍጢር ሕብረትንና አንድነትን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁሉም ኃይማኖቶች በፍቅርና በመተባበር ለሀገር ልማትና እድገት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።