የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል
ጂንካ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት መገኘቱን የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሰለ ገለፁ።
ሴቶች ለማኅበረሰብ ለውጥ ያላቸውን ትጋት በሀገረ መንግስት ግንባታም ሊያጠናክሩት ይገባል
በጂንካ ዩኒቨርስቲ "50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለፀገች ኢትዮጵያ "በሚል መሪ ሀሳብ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የዕለቱ የክብር እንግዳና የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሰለ እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ አመታት የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ ብሎም የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አበረታች ለውጦች ታይተዋል።
ሴቶች የመሪነት ሚናቸው እና ውሳኔ የመስጠት አቅማቸው እያደገ መምጣቱን አንስተው፥በሀገረ መንግስት ግንባታውም ሚናቸው እየጎላ መምጣቱን ጠቁመዋል።
ሴቶች ያላቸውን እምቅ አቅምና ዕውቀት ለሀገረ መንግስት ግንባታና ለማህበረሰብ ለውጥ ማዋል እንዲችሉ መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባም አንስተዋል ።
በተለይ ሴት ምሁራን አርአያና በጫና ውስጥ ላሉ ሴቶች ብርሃንና ተስፋ ናቸው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ፥ ሴት ምሁራን በርካታ ተተኪ ሴቶችን በማፍራት ወደፊት እንዲመጡ ማበረታት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የጂንካ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ ይትባረክ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው ተሳትፏቸውን ይበልጥ ለማሳደግ የበለጠ ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ሴት ልጅን ማስተማር ሀገር ማስተማር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፥ያለ ሴቶች ተሳትፎ ሀገራዊ እና ማህበራዊ እድገት፣ለውጥና ብልጽግና አይታሰብም ብለዋል።
የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ከሚጎትቱ ተግባራት አንዱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመው፥በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስወገድ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ጂንካ ዩኒቨርሲቲም በተለይ በአርብቶ አደሩ አከባቢ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና ውሳኔ ሰጪነት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በጥናትና ምርምር በመለየትና የመፍትሔ ሀሳብ በማመላከት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወይኒቱ መልኩ፤የክልሉ ሴቶች በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፍች ተሳታፊነታቸውና ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል ።
ቀደም ሲል በተለይ በገጠሩ አካባቢ የሴቶች የሀብት ባለቤትነት የተገደበ መሆኑን አንስተው ፥ ከለውጡ አመታት ወዲህ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተደረገው ርብርብ ሴቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ከመሳተፍ አልፎ በትላልቅ ኢንቨስትመንቶች በመሳተፍ ሀብት ማፍራት ጀምረዋል ብለዋል።
በመድረኩ በዩኒቨርስቲው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል።