ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ያጠናክራል

ነቀምቴ፤ መጋቢት 03/2018 (ኢዜአ)፦ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እንደሚያጠናክር ገለጸ።

በለውጡ ዓመታት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ የምስራቅ ወለጋ ዞን እና የነቀምቴ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ጽሕፈት ቤቶች በጋራ ባዘጋጁት መድረክ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።


 

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተስፋዬ ለማ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት እያከናወነ ነው። 

በተለይም በዩኒቨርሲቲው የሴት ምሁራንን አቅም በማጎልበት በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሴቶች በሳይንሳዊ ምርምር፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በማህበረሰብ አገልግሎት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ለሀገር ግንባታና ብልጽግና ወሳኝ በመሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲው ሴቶችን በማብቃትና ምቹ የሥራ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ  የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ያጠናክራል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሀሊማ ጅብሪል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የሴት መምህራንን እና ተማሪዎችን አቅም የሚያሳድጉ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የዓለም የሴቶች ቀን መከበርም በሴቶች የተመዘገቡ ድሎችን ለማስቀጠልና በሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ሴቶችና ሕፃናት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ሞሲሳ በበኩላቸው፤ ቀኑ ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በአመራርና በትምህርት ዘርፎች ያላቸውን እኩል ተሳታፊነት ለማሳደግ ታስቦ የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል።


 

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በሰጡት አስተያየት፤ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አከባበር ከውይይትና ከምክክር ባለፈ በተግባር የሚታዩ ለውጦችን በማስመዝገብ ረገድ ትልቅ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም