ቀጥታ፡

በለውጡ ዓመታት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው

ወላይታ ሶዶ ፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸው ተገለፀ።

የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ውጤት ተገኝቷል

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን "50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሐሳብ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ  ሴት ምሁራን በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።


 

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሺመቤት ነጋሽ በወቅቱ እንዳሉት፤ የለውጡ መንግስት የሴቶችን ጉዳይ ከመሠረታዊ የመብት ጥያቄዎች ወደ ፖሊሲና ስትራቴጂክ ጥያቄዎች በማሸጋገር ስኬታማ ተግባራትን አከናውኗል።

ሴቶች በሳይንስና ፖሊሲ ቀረፃ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ የተሰራው ስራም ውጤታማ መሆኑንም ነው የገለጹት።


 

በአሁኑ ወቅትም ሴቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ያላቸውን አቅም በተሻለ መንገድ እንዲያሳዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ነው የጠቀሱት።

''ሴቶችን ማክበር ሀገርን ማክበር ነው ያሉት ደግሞ'' የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር ተመስገን ገብረ እየሱስ ናቸው።

ሴቶች የውሳኔ ሰጪነት ቦታ የተነፈጉበት ታሪክ አብቅቶ በሁሉም ዘርፎች ብቃታቸውን እንዲያሳዩ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀማቸው በየመስኩ ተሳትፏቸው እያደገ እንዲመጣ አድርጓል ነው ያሉት።


 

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲም ሴቶች የሚገጥሟቸው ችግሮች እንዲቃለሉ ከመስራት ባለፈ ወደ አመራርነት እንዲመጡ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በርካታ ሴቶች የአመራርነትና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም ነው የጠቀሱት።

ሴቶች ሀገር በመጠበቅና ጠላትን በመመከት በዓድዋ ያሳዩትን የአርበኝነት ተጋድሎ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ መድገም አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል።

በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወላይቴ ቢቶን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልል ፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የዩኒቨርስቲ ሴት ምሁራንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም