ሴቶች ለማኅበረሰብ ለውጥ ያላቸውን ትጋት በሀገረ መንግስት ግንባታም ሊያጠናክሩት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች ለማኅበረሰብ ለውጥ ያላቸውን ትጋት በሀገረ መንግስት ግንባታም ሊያጠናክሩት ይገባል
ሚዛን አማን፤ መጋቢት 3/2018(ኢዜአ)፦ ሴቶች ለማኅበረሰብ ለውጥ ያላቸውን ትጋት በሀገረ መንግስት ግንባታም ሊያጠናክሩ ይገባል ሲሉ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ሉባባ ጀማል ገለጹ።
"50ኛ ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ የሴቶች ቀን በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል።
በመድረኩ የተገኙት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ሉባባ ጀማል እንዳሉት ሴቶች ባላቸው እውቀትና የማድረግ አቅም ባለፉት ጊዜያት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል።
ሴት ምሁራን ለማኅበረሰብ ለውጥ ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወቱ ጠቅሰው በሳይንስና በፖሊሲ ቀረፃ ላይ ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዛሬ በዩኒቨርሲቲው ከሴት ምሁራንና አመራሮች ጋር የምናከብረው የሴቶች ቀን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለተሰሩ ውጤታማ ሥራዎች እውቅና ለመስጠትና ፕሮጀክቶቻቸውን በተግባር ለማሳየት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እኩልነትን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሴቶች ማድረግ እንደሚችሉ የሚያሳዩበት ሥነ ምህዳር ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
ሴቶች በውሳኔ ሰጭነት ላይ ያላቸው ሚና እንዲጠናከር ሴት ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ጥናት፣ ምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዚዳንት ግርማ ጥላሁን(ዶ/ር) ሴቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና በብቃት የመወጣት ብቃት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ "የኢትዮጵያ ሴት ምሁራን ሚና በሀገረ መንግሥት ግንባታ" በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው መምህርት አስካለ ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ሴቶች ብዙ ጫናዎችን ተሻግረው በስኬት ሀገርንና ህዝብን እያገለገሉ ነው ብለዋል።
በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ለማኅበራዊ ሕይወት ጫና ሳይበገሩ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ክህሎት አውጥተው ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም የሴቶችን ጀግንነት የሚያወሳ ትርክት መገንባትና የብርቱ ሴቶችን ታሪክ ሰንዶ ማስተላለፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።