ቀጥታ፡

በተጠባቂው ጨዋታ ሪያል ማድሪድ ማንችስተር ሲቲን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ መርሐ-ግብር ሪያል ማድሪድ ማንችስተር ሲቲን 3 ለ 0 ረቷል።



በበርናባው ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፌዴሪኮ ቫልቫርዴ በ20ኛው፣ በ27ኛው እና በ42ኛው ደቂቃ ግቦቹን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።

ባየር ሌቨርኩሰን እና አርሰናል አቻ ተለያዩ

ሪያል ማድሪድ በ58ኛው ደቂቃ ያገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ቪኒሺየስ ጁኒየር መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

በጨዋታው ሪያል ማድሪድ በተጋጣሚው ላይ ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል።

ግልጽ የግብ እድሎችን መፍጠር ያልቻለው እና የተከላካይ ክፍሉ ስህተት ሲሰራ የነበረው ማንችስተር ሲቲ ደካማ እንቅስቃሴ አድርጓል።

ኪሊያን ምባፔ እና ጁድ ቤሊንግሃምን ጨምሮ ቁልፍ ተጫዋቾቹን በጉዳት ምክንያት ወደ ሜዳ ይዞ ያልገባው ሪያል ማድሪድ ጠንካራ ብቃት አሳይቷል።

ውጤቱን ተከትሎ የ15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ማድሪድ ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ እድሉን አስፍቷል።

ማንችስተር ሲቲ በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን የመቀልበስ ከባድ የቤት ስራ ይጠብቀዋል።

 

በሌላኛው መርሐ-ግብር የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ቼልሲን 5 ለ 2 አሸንፏል።

በፓርክ ደ ፕሪንስ በተደረገው ጨዋታ ክቪቻ ክቫራትስኬሊያ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር
ብራድሊ ባርኮላ፣ ኡስማን ደምበሌ እና ቪቲንሃ ቀሪዎቹን ጎሎች ለፈረንሳዩ ክለብ ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ማሎ ጉስቶ እና ኢንዞ ፈርናንዴዝ ለቼልሲ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

ፒኤስጂ ወደ ሩብ ፍጻሜ የመግባት እድሉን የበለጠ ሰፊ አድርጓል።

 

ቦዶ ግሊምት ስፖርቲንግ ሊዝበንን 3 ለ 0 አሸንፏል።

በአስፕማይራ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኦሌ ብሉምበርግ እና ካስፐር ዋርትስ ሆግ በጨዋታ፣ ሶንድሬ ብሩንስታድ ፌት በፍጹም ቅጣት ምት ግቦቹን አስቆጥረዋል።

በሻምፒዮንስ ሊጉ ጥሩ ግስጋሴ እያደረገው የሚገኘው የኖርዌው ክለብ ቦዶ ግሊምት ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ እድሉ ሰፊ ሆኗል።

ዛሬ አስቀድሞ በተደረገ ጨዋታ ባየር ሌቨርኩሰን እና አርሰናል አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ስድስቱ የእንግሊዝ ክለቦች ማሸነፍ አልቻሉም።

የጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታዎች በቀጣዩ ሳምንት ይደረጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም