ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉን በመከተል የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ተዘጋጅተናል

አዳማ ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ሥነ ምግባር ሕጉን በመከተል የተሰጣቸውን  ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የአዳማ ከተማ ወጣቶች ፌዴሬሽን  ገለጸ።

ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ 47 የተለያዩ ፓርቲዎች በድምሩ 1 ሺህ 934 ዕጩዎችን ያስመዘገቡ ሲሆን፣ በመቀጠልም የመራጮች ምዝገባ ተጀምሮ በሂደት ላይ ይገኛል። 

በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አካሄድ እንዲጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን - የፖለቲካ ፓርቲዎች

ለጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊነት የፓርቲዎች ዝግጁነት እንዳለ ሆኖ፣ በተለይም ደግሞ የሲቪክ ማኅበራት ሚና ወሳኝ መሆኑ ይታመናል።

በዚህም መሠረት የአዳማ ከተማ ወጣቶች ፌዴሬሽን፤ በገለልተኝነት ለማገልገልና በተለይም ወጣቶች በምርጫው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። 

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ወጣት ሲሳይ አበራ እንደገለጸው፤ ፌዴሬሽኑ ከከተማዋ የወጣቶች ማኅበር ጋር በመተባበር በምርጫ ሥነ ምግባር፣ ሕጎችና ደንቦች ላይ ለአባላቱ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በምርጫ ታዛቢነት፣ በመራጭነትና በአስመራጭነት ወጣቶች በንቃት እንዲሳተፉ በምርጫ ሥነ ምግባር፣ ሕጎችና ደንቦች ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲል ተናግሯል። 

ፌዴሬሽኑ በምርጫ ታዛቢነት አባላቱ እንዲሳተፉ ተሳታፊዎችን በመምረጥ ዝርዝራቸውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መላኩን ገልጾ፤ ለምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብሏል። 

በመሆኑም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በገለልተኝነት ለማገልገልና በመምረጥ የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጧል።

የአዳማ ከተማ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ወጣት አብደላ ጌሎ በበኩሉ፤ በከተማ፣ በዞንና በወረዳዎች ያሉትን አደረጃጀቶች በማስተባበር ምርጫው ፍትሐዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን ማኅበሩ እየሠራ ይገኛል ብሏል።


 

በከተማ አስተዳደሩ ሥር በሚገኙ 185 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ማኅበሩና ፌዴሬሽኑ በጋራ በመሆን የምርጫ ታዛቢዎችን መርጠው ማዘጋጀታቸውንም ተናግሯል።

በምርጫ ታዛቢነት፣ በመራጭነትና በአስመራጭነት ሊኖራቸው የሚገባውን ሥነ ምግባር፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሥልጠናና አቅም ግንባታ ሥራ መከናወኑን ገልጿል። 

በሚመደቡባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሥነ ምግባርንና ሕጉን በመጠበቅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል። 

በመራጭነት ወጣቶች በንቃት እንዲሳተፉ በኦንላይንና በአካል በየምርጫ ጣቢያው በመቅረብና በመመዝገብ የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ ግንዛቤ የመፍጠርና የንቅናቄ ሥራ እየሠራን እንገኛለን ነው ያለው።


 

የአዳማ ወጣቶች ማኅበር አባል ሳራ ሙሐመድ፤ በየደረጃው ያለን የማኅበሩ አባላት በምርጫ ሥነ ምግባርና ደንቦች ላይ ግንዛቤ አግኝተናል በማለት ተናግራለች። 

በመሆኑም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በነቂስ ለመሳተፍ የሚያስችል በቂ ግንዛቤ አግኝተን የሚጠበቅብንን ለመወጣት እየሠራን ነው ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም