ቀጥታ፡

በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አካሄድ እንዲጠናከር የበኩላችንን እንወጣለን - የፖለቲካ ፓርቲዎች

ሚዛን አማን፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አካሄድ እንዲጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

በክልሉ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

በግንቦት ወር ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ይህንንም በተመለከተ ኢዜአ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አነጋግሯል፡፡

ፓርቲዎቹም የምርጫ ሥነ ምግባር ህጉን በተከተለ አግባብ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አስተባባሪ እና የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ጎዳናው ሙንኤ እንዳሉት፤ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ  ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች የተሻለ ነው።

እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የተሻለ ሀሳብ ብቻ ለመራጩ ሕዝብ በማቅረብ በሀሳብ ልዕልና ላይ ተመርኩዞ የማሸነፍ አካሄድ እንዲጠናከር የበኩላችንን ሚና ለመወጣት እየተዘጋጀን ነው ብለዋል።

ለዚህም ምርጫው በሕዝብ ድምጽ ብቻ የሚወሰን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በጋራ ምክር ቤት ተግባብተው ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሕዝቡ ተመዝግቦ ካርድ እንዲወስድ የማስተባበር እና የመቀስቀስ ሥራ እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ዘለቀ ናቸው።


 

የዘንድሮው ምርጫ በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ የተሻለና ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸው ዴሞክራሲያዊ እና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ተከትለን እየሰራን ነው ብለዋል።

የምርጫው ሂደት ፍትሐዊ፣ አካታችና በሕዝብ ድምጽ ብቻ የሚወሰን እንዲሆን በመሥራት ውጤቱን ሕዝብና ሀገርን ባከበረ መልኩ ለመቀበል እየተዘጋጀን ነው ብለዋል።

የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ባሻ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን  በሀሳብ ልዕልና ለማሸነፍ እየሰራን ነው ብለዋል።


 

በተለይም ፓርቲዎች በጋራ በመነጋገር የሚያጋጥማቸውን ችግር እየፈቱ ሂደቱን እያስቀጠሉ መሆናቸውን ጠቅሰው የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ሥነ ምህዳር አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ማንኛውንም ችግር በጋራ ምክር ቤቱ በኩል ለመፍታት መግባባት ላይ ተደርሶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ይህም መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የፈጠረውን ምቹ ሥነ ምህዳር የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም