የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ችግሮችን በምክክርና በውይይት የመፍታት ባህልን እያዳበረ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ችግሮችን በምክክርና በውይይት የመፍታት ባህልን እያዳበረ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ችግሮችን በምክክርና በውይይት የመፍታት ባህልን እያዳበረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የአገረ መንግሥት ግንባታን ለማጽናት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለዘመናት የዘለቁ ቅሬታዎችን በውይይት ለመፍታትና ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታን እውን ለማድረግ ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እስካሁን በተለያዩ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በተከናወኑ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ዳያስፖራዎች ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል።
ይህም ለችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ የምክክር ባህል እንዲዳብርና በዜጎች መካከል እምነት እንዲገነባ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
በአማራ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ቆይተው የሰላም አማራጭን የተቀበሉ አካላት አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ ማስረከባቸው ለሂደቱ ስኬታማነት ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
ይህ ተግባር ሀገራዊ ችግሮችን በምክክርና በሰላማዊ ውይይት መፍታት እንደሚቻል በተግባር ያሳየና ዜጎች በምክክሩ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዲሰንቁ ያደረገ መሆኑንም ዶ/ር ዮናስ ገልጸዋል።
አካታችነትን ማረጋገጥ የኮሚሽኑ ቀዳሚ መርህ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዜጎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ ሰፋፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል የተካሄዱ የቅድመ ምክክር መድረኮች ሂደቱን ሙሉ በሙሉ አካታች ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
በቀጣይም በክልሉ የተሟላና ሁሉን አቀፍ ምክክር ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ መራዘም የተጀመሩ ተግባራትን ይበልጥ በጥራትና በስኬት ለማጠናቀቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
አጀንዳዎችን በማጠናቀር ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ፣ በትግራይ ክልል የተጀመረውን የምክክር ሂደት በስኬት ለማጠናቀቅና ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን በታቀደው መሠረት ለማካሄድ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
እንዲሁም የመጨረሻውን የምክክር ውጤት በዝርዝር አዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡