ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የአገረ መንግሥት ግንባታን ለማጽናት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠርና የአገረ መንግሥት ግንባታን ለማጽናት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የዴሞክራሲ ባህልን በማዳበር ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚያንጽ ወሳኝ መድረክ ነው

"የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት እመርታ፤ ለተሳካ ሀገረ መንግሥት ግንባታ!" በሚል መሪ ሀሳብ በዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅት ላይ የሚያተኩር ሀገራዊ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

መድረኩ በዋናነት በሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት እና በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ተቋማት ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመነሳት በቀጣይ ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ በሚያረጋግጡባቸው ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መክሯል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና አገረ መንግሥቱን ለማጽናት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ 

መንግሥት መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት ኮሚሽኑን በማቋቋም ማሳየቱን ገልጸዋል። 

ኮሚሽኑን ከመመሥረት ጀምሮ የነበረው ሂደት ግልጽና ገለልተኛ እንዲሆን የተከናወኑ ተግባራት ለምክክሩ ሂደት ተዓማኒነት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል። 

ተቋም መገንባት አገረ መንግሥቱን ለማጽናትና ለመገንባት እጅግ ወሳኝ ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው ኮሚሽኑ ለዚህ ዓላማ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ ኮሚሽኑ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እስካሁን ውጤታማ የሚባሉ ሥራዎችን ሰርቷል። 

አካታችና የዜጎች ተሳትፎ የተረጋገጠበት የምክክር ሂደት በማካሄድ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራውን በአስራ አንድ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ መስተዳደሮች ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል፡፡ 

የምክክሩ ሂደት ነፃ፣ ገለልተኛ እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የጎላበት እንዲሆን ማድረግ የኮሚሽኑ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ውጤታማ ስራዎችን ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በተከናወነው የተሳታፊዎች ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር ከታቀደው ውስጥ 93 በመቶውን ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ 

በቀጣይም አጀንዳ መቅረጽና ይፋ ማድረግ እንዲሁም ሀገራዊ ምክክር ማካሄድን ጨምሮ ሌሎችም ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም