ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካዊነት እሳቤ እንዲጎለብት የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች

ሀዋሳ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ጽኑ መሰረት እንዲይዝና የፓን አፍሪካዊነት እሳቤ እንዲጎለብት የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ መቀጠሏን የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

በአፍሪካ የምጣኔ ሃብት፣ የባህልና የፖለቲካ ትስስርን ማጠናከርና አማርኛን ከህብረቱ የስራ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምሁራን የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ስትራቴጂካዊ አቅም ይፈጥራል

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፍጮ፤ ኢትዮጵያ ከአፍርካ አንድነት ድርጅት ምስረታ እስከ አሁኑ የአፍሪካ ህብረት ያላት ሚና የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

በአፍሪካ ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠርና የአህጉሪቷ መሪዎች በተደመረ አቅም ለጋራ እድገትና ብልፅግና እንዲተጉ በማድረግ ረገድ ከጥንት እስካሁንም ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አህጉራዊ እድገትና ብልጽግናን እውን ከማድረግ በተጓዳኝ የአፍሪካ የተሳሳተ ትርክት መቀየር አለበት የሚል ፅኑ አቋም በመያዝ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ትስስር እንዲፈጠር በመስራት ረገድ የላቀ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጸው ከዚህ አንፃር አማርኛን የህብረቱ የሥራ ቋንቋ ማድረግ አህጉራዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልሳን ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም፤ በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ አማርኛ ስነ-ጽሁፋዊና ስነ-ልሳናዊ ቅርስ ያለው መሆኑ የህብረቱ የስራ ቋንቋ ቢሆን ለአባል አገራቱ ጥሩ ልምድና ተሞክሮ የሚገኝበት ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የቋንቋ ፖሊሲ ይህን የሚያጠናክር መሆኑን አውስተው ጥረቶቹ መጠናከር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ሌላኛው ጽሁፍ አቅራቢ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስነ ልሳንና ስነተግባቦት ተባባሪ ፕሮፌሰር ፈቀደ ምኖታ (ዶ/ር)፤ ለህብረቱ ከኢትዮጵያ የስራ ቋንቋ መጠቀም በብዙ መልኩ አህጉራዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የፓን አፍራካኒዝም እሳቤን ከማጎልበት ባለፈ በአህጉሪቷ ጠንካራ ማህበራዊ፣ የምጣኔ ሃብትና የፖለቲካ ትስስር እንዲፈጠር ይበልጥ ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም