የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ስትራቴጂካዊ አቅም ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ስትራቴጂካዊ አቅም ይፈጥራል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ስትራቴጂካዊ አቅም እንደሚፈጥር በመከላከያ ሰራዊት የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን ገለጹ።
ብሔራዊ የኢትዮጵያ ሰራዊት ማህበር ቀይ ባሕርና የባሕር በር ለኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ መብት በሚል መሪ ሐሳብ ውይይት እያካሄደ ነው።
በመከላከያ ሰራዊት የትምህርትና ስልጠና ዋና መመሪያ ሃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ከአክሱም ስልጣኔ ጀምሮ አዱሊስና ዛይላ የኢትዮጵያ የንግድና የባህል በር ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር ታሪክ የሚያስረዳው ሀቅ ነው።
ይህ ታሪካዊ ሀቅ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ጥያቄ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ፍላጎት ሳይሆን ከሉዓላዊነትና ከብሔራዊ ህልውናዋ ጋር የተጋመደ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ከባሕር በር እንድትገለል መደረጉ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማነቆ መሆኑን ገልጸው የባህር በር ጥያቄው ምላሽ ማግኘት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብሎም ለቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባሕር በር ባለቤትነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ በአካባቢው የሚታዩ የፀጥታ ስጋቶችን በጋራ መከላከል የሚያስችል ስትራቴጂካዊ አቅም የሚፈር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነትንና ቀጣናዊ ውህደትን መሰረት ያደረገ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የጋራ ተጠቃሚነት ትብብር፡ በቀጣናው ሰላምና የመሰረተ ልማት ትስስርን በማጠናከር የምስራቅ አፍሪካን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የነቃ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ጠቁመው ለዚህም የማህበሩ አባላት ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የብሔራዊ የኢትዮጵያ ሰራዊት ማህበር ፕሬዝዳንት ሀምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ በበኩላቸው፤ የማህበሩ አባላት በሀገር ጉዳይ ላይ ግንባር ቀደም ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የባሕር በር ጥያቄም በሰለማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ ማህበሩ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።