የሃይማኖት ተቋማት ለክልሉ እድገት የሚተጉ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነታቸውን ማጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማት ለክልሉ እድገት የሚተጉ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነታቸውን ማጠናከር አለባቸው
ሆሳዕና፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ የሃይማኖት ተቋማት ለክልሉ እድገት የሚተጉ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) አሳሰቡ።
የሃይማኖት ተቋማት አንድነታቸውን በማጠናከር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ያላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል
“በመደመር መንግሥት እይታ፣ የሃይማኖት ተቋማት ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ምዕመናን የተዘጋጀ ክልል አቀፍ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ የምክክር መድረኩን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፤ የሃይማኖት ተቋማት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ለክልሉ ፈጣን ዕድገት መረጋገጥ የሚያውሉ ዜጎችን ማፍራት ይጠበቅባቸዋል።
መንግሥት አገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ያሳተፈ ተግባር በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የሃይማኖት ተቋማትም ሰላምን በማረጋገጥና በክልሉ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በሥነ-ምግባር የታነጹ ዜጎችን በማፍራት የሀገረ መንግሥት ግንባታው እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱም ጠቁመዋል።
በተለይም በማኅበረሰቡ መካከል መከፋፈልንና ግጭቶችን ለማስፋት የሚሰሩ አካላትን በማረም ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ትልቅ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ በሁሉም መስክ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማጠናከር የሁሉም ርብርብ መጠናከር አለበት ብለዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት ተቋማት የሕዝቦችን ሰላምና አብሮነት ለማጠናከር በሚረዳ መልኩ ለትውልድ ግንባታ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የቤተ እምነቱ መሪዎችና ምዕመናን እየተሳተፉ ይገኛሉ።