የሃይማኖት ተቋማት አንድነታቸውን በማጠናከር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ያላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማት አንድነታቸውን በማጠናከር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ያላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፦የሃይማኖት ተቋማት አንድነታቸውን በማጠናከር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ያላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለፀ።
በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች " የመደመር መንግስት በሃይማኖት ተቋማት ላይ ያለው ዕይታ አስተዳደራዊ መርሆዎች፤ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን "አስመልክቶ ከኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አባቶች ጋር የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል፡፡
በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እንዳሉት፤ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የቤተ-ክርስቲያን ድርሻ ከፍ እንዲል ይጠበቃል።
የሃይማኖት ተቋማት መጠናክር ለሀገረ መንግስት ግንባታ ምሰሶ በመሆናቸው ይህንኑ ተቋማዊ አንድነት ማጠናክር እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
ቤተ-ክርስቲያን በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ የመቅረጽ ሚናዋን መወጣት፣ የጥላቻ ንግግሮችን ማውገዝ እንዲሁም ቤተ-ክርስቲያንን መሸሸጊያ የሚያደርጉ ኃይሎችን ማስተማር እንዳለባትም አሳስበዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማዋ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፤የሃይማኖት ተቋማት ትውልድን በማነጽ፣ በሀገር ሰላምና ግንባታ ላይ የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቲዮስ፤ እንደ ሀገር የተጀመሩ የሰላምና የብልጽግና ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሃይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የከተማዋን ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ የገለፁት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበሩ (ዶ/ር) ናቸው።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደደር የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብድልቃድር ሬድዋን የሃይማኖት ተቋማት ለሀገር ሰላም መረጋገጥ የላቀ አስተዋፅኦ አላቸው ብለዋል።
በመድረኩ አስተያየት የሰጡ የሀይማኖት አባቶች በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናትና ቅርሶችን ለመንከባከብ በርካታ ስራዎችን መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
ይህም መንግስት ለዕምነት ተቋማት እና ለህዝቡ ያለውን አክብሮት እንደሚያሳይ አንስተው በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎች የጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ከመንግስት ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡