ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን ድርቅንና የአካባቢ መራቆትን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችሉ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

ነጌሌ ቦረና ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በዘንድሮው ዓመት ለሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድርቅንና የአካባቢ መራቆትን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችሉ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል የተሻሻሉና የአካባቢን ስነ-ምህዳር ታሳቢ ያደረጉ የቡና ችግኞች ይተከላሉ

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ ወንዶ ሸርቦቴ ለኢዜአ እንዳሉት፤በዘንድሮ የክረምት ወቅት ለሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድርቅንና የአካባቢ መራቆትን ለመቋቋም የሚያስችሉ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው።

የችግኝ ዝግጅቱ በዞኑ ባሉ ከ170 በላይ ችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እየተካሔደ ሲሆን እስካሁን ባለው ሒደት 89 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት መቻሉን አስታውቀዋል።


 

ይህም በየዓመቱ የሚከሰተውን ድርቅና የአካባቢ መራቆት ችግርን በዘላቂነት ለመቋቋም እንደሚያስችል ታምኖበታል ነው ያሉት።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል የሆነው የችግኝ ዝግጅቱ የጉጂ ዞንን ደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላማ የአየር ንብረት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አውስተዋል።

ለተከላ ከተዘጋጁት የችግኝ ዝርያዎች ውስጥ ጽድ፣ ግራቪሊያ፣ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባና ሌሎችም እንደሚገኙበት ነው ያመለከቱት።

እንዲሁም ለከተማ ውበት፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለምግብነት የሚውሉና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሙዝና ግሽጣ ያሉ ፍራፍሬዎችን ያካተተ የችግኝ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።

ችግኞቹን ለማልማትና ለውጤት ለማብቃት ከሰውና ከእንስሳት የተከለለ ከ21 ሺህ 340 ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን  አስረድተዋል።


 

በመጪው ክረምት በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ስራ ከ205 ሺህ በላይ ህዝብ ለማሳተፍ የቅስቀሳና የግንዛቤ ማሳደግ ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት ከተተከሉት ችግኞች በህዝብ እንክብካቤና ጥበቃ 83 በመቶው መጽደቁን በመስክ ምልከታና ክትትል ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም