በአማራ ክልል በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ዜጎች የቴክኖሎጂ ክህሎት እንዲታጠቁ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ዜጎች የቴክኖሎጂ ክህሎት እንዲታጠቁ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ባህር ዳር ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ዜጎች ከወቅቱ ጋር የሚጓዝ የቴክኖሎጂ ክህሎት እንዲታጠቁ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።
በኢትዮ ኮደርስ ኢንሼቲቭ ከ570 ሺህ በላይ ዜጎችን በማሰልጠን ከታቀደው በላይ ለመፈፀም በሚያስችል አግባብ እየተከናወነ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በክልሎቹ የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ የማድረጉ ተግባር ውጤት እያመጣ ነው
በኢትዮ ኮደርስ ኢንሼቲቭ እንደ ሃገር 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን የቴክኖሎጂ ስልጠና እንዲወስዱ ግብ ተይዞ እየተተገበረ ይገኛል።
ስልጠናውም ትውልዱን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ስራዎችን ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያግዝ እንደሆነም ታምኖበት እየተተገበረ ይገኛል።
በአማራ ክልልም ስልጠናው ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተሰጠ ሲሆን በዚህም በርካቶች ስልጠናውን በመውሰድ እየተጠቀሙበት ይገኛል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ቴክኖሎጂዎች በፍጥነት የሚያድግና ተለዋዋጭ በመሆኑ ከዚሁ ጋር አብሮ መጓዝን ይጠይቃል።
በክልሉ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 791 ሺህ የሚደርሱ ዜጎችን ለማሰልጠን ዕቅድ ተቀምጦ እየተሰራ ሲሆን እስካሁን ባለው ከ570 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠና መውሰዳቸውን አስረድተዋል።
ይህም የእቅዱን 72 በመቶ ማሳካት መቻሉን እንደሚያመላክት አብራርተዋል።
በቀሪ ጊዜያት ስልጠናውን በመስጠት ዜጎች ከወቅቱ ጋር የሚጓዝ የቴክኖሎጂ ክህሎትን እንዲታጠቁ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው አረጋግጠዋል።
በኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ እና ዳታ አናሊስስን ጨምሮ በአራት ዘርፎች በመሰልጠን የምስክር ወረቀት ባለቤት መሆኑን የገለፀው ደግሞ ብርሃኑ አሰፋ ነው።
በዚህም ከዘመኑ ጋር ለመጓዝ የሚያስችል እውቀት ማግኘቱን ጠቅሶ፤ ሌሎች የእድሉ ተጠቃሚ ያልሆኑ ወገኖችም በስልጠናው ሊሳተፉ እንደሚገባ አመልክቷል።
ሲሳይ ይመር የተባለ ሰልጣኝ በበኩሉ፤ ቴክኖሎጂን በተግባር በመለማመድ የሙያ ባለቤት መሆን መቻሉን ነው የገለጸው።
በተለይም ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በተያያዘ ሰፊ እውቀት ማግኘቱን ጠቅሶ፤ ስልጠናውም አሁን እየሰራ ያለውን ስራ በጥሩ ሁኔታ እንዳገዘውም ተናግሯል።