በክልሎቹ የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ የማድረጉ ተግባር ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሎቹ የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ የማድረጉ ተግባር ውጤት እያመጣ ነው
አዳማ፤ መጋቢት 1/2018(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የከተሞች አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ የማድረጉ ተግባር ውጤት እያመጣ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሎቹ የዘርፍ የስራ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንደገለጹት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የተገልጋይነት እርካታን ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጨምር ኃይሌ እንደገለጹት፤ በክልሉ የአገልግሎት አሰጣጡን ከወረቀት ንክኪ ነፃ በማድረግ ወደ ዲጂታል ስርዓት ለማስገባት ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል።
በተለይም በመሬት፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር እንዲሁም የገቢዎችን ዘርፍ ጨምሮ 55 የሚሆኑ አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ መሰጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
የዲጂታል አገልግሎቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ በሆሳዕና፣ በቡታጂራ፣ በወልቂጤ፣ በዱራሜ፣ በወራቤ፣ በአላባ ቁሊቶና በሳጃ ከተሞች የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በ16 ከተሞች በዲጂታል ዘዴ የታገዘ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥን ወደ 24 ከተሞች ለማሳደግ የተጀመረው ስራ ይጠናከራል ብለዋል።
አቶ ጨምር አክለውም የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሶፍትዌሮችን በማቅረብ እና የዲጂታላይዜሽን ስራውን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ይህም የመረጃ አያያዝን ከማዘመኑም ባለፈ፣ ፋይል ለመፈለግ ይባክን የነበረውን ጊዜና የተገልጋዮችን ቅሬታ መቀነስ መቻሉን፣ እንዲሁም የሊዝ እዳ መረጃን በአግባቡ ለማወቅና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የከተማ ልማት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ቢፍቱ ጎሹ፤ በክልሉ ከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በመሬት እና በገቢዎች ዘርፍ ያሉ ፋይሎችን ወደ ሶፍት ኮፒ የመቀየር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በስምንት ማዕከላት ለማስጀመር እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።
በአሶሳ ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ለመጀመር የግንባታና የፋይሎችን መረጃ ወደ ዲጂታል የማስገባት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ኢንጂነር ቢፍቱ አክለዋል።