ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተናል-የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅተናል-የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ወጣቶች
ጭሮ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የሚገኙ ወጣቶች ገለጹ።
ዜጎች የመራጮች ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል
በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እንደሀገር የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ማከናወን ይገባል።
ለዚህም የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ወጣቶቹ፣ ለምርጫው ስኬታማነት ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ሀብሮ ወረዳ ገለምሶ ከተማ የሚኖረው ወጣት ሐኪም አብደላ፤ ጠቅላላ ምርጫው ስኬታማ መሆን እንደሀገር በሁሉም መስኮች የተጀመረው የልማትና የለውጥ ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው ወሳኝ በመሆኑ የምርጫ ካርድ ወስዶ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም መዘጋጀቱን ገልጿል።
በመምረጥ ከሚያደርገው ተሳትፎ ባለፈ ህብረተሰቡን የማንቃትና የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሰራም ነው የገለጸው።
እንደ ወጣት ሐኪም ገለጻ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ ሆኖ የሀገርን መልካም ገጽታ እንዲገነባ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።
ምርጫው በሁሉም ረገድ የተሳካ እንዲሆን እንደ አንድ ዜጋ ከእኔ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ያለው ደግሞ ወጣት አህመድ ኢብሮ ነው።
ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ባህል እንዲጎለበት ከማድረግ ባለፈ ህዝቡም ይጠቅመኛል ለሚለው አካል ድምጹን በነጻነት እንዲሰጥ ያለው ሚና የጎላ በመሆኑ በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ግዴታውን እንደሚወጣ ተናግሯል።
ወጣቶች በምርጫው ያላቸው ተሳትፎና የመሪነት ሚና እንዲጎለብት በየደረጃው ካሉ የወጣት አደረጃጀቶች ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ገልጿል።
የጭሮ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ሮዛ አብደላ በበኩሏ፤ ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው መጻኢ እድልና ተስፋ ላይ ውሳኔያቸውን የሚሰጡበት የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ በመሆኑ ሁላችንም ንቁ ተሳታፊ ልንሆን ይገባል ብላለች።
በምርጫ ሂደት ወጣቶች እንደ አንድ የህብረተሰብ ክፍል ጉልህ ሚና መጫወት አለብን የምትለው አስተያየት ሰጪዋ በምርጫው ይሆነኛል የምትለውን ከመምረጥ ባለፈ ለምርጫው ሰላማዊነትና አሳታፊነት የበኩሌን እወጣለሁ ብላለች።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ አገሪቱ ከጀመረችው የለውጥ ጎዳና አንፃር ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው የተናገረችው ደግሞ የሂርና ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ሮዛ ያሲን ናት።
ምርጫው ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁማ፣ ምርጫው በላቀ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲሳካ በባለቤትነት መንፈስ ለመሳተፍ መዘጋጀቷን ገልጻለች።