ዜጎች የመራጮች ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎች የመራጮች ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል
ሮቤ ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ሳይዘናጉ የመራጮች ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል ሲሉ የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ለፆታ እኩልነትና ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚሰራ ፓርቲን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል- ሴቶች
በከተማዋ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በአሁኑ ወቅት በንቃት እየተካሄደ ይገኛል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ምርጫው ለአገር ዕድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና እንዳለው በመረዳት በምርጫው ለመሳተፍ ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ መልያ አደም፤ ለሀገሪቱ የሚበጀውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ዜጎች ሳይዘናጉ የመራጮች ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት ካርድ በመውሰድ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል።
ሌላው አቶ አብዱልጀባር አልይ፤ ምርጫ የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ መሆኑን በተግባር የሚታይበት ሂደት መሆኑን ተገንዝበው የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፣ ካርድ ያልወሰዱ ሌሎች ነዋሪዎችም እንዲመዘገቡ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የምርጫ ካርድ መውሰድ ለሀገር ይበጃል የሚሉትን አካል ለመምረጥ ወሳኝ መሆኑን በማንሳት ለሂደቱ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ አብዱልቃድር ሁሴን ናቸው።
ወይዘሮ ሀልማ አልይ በበኩላቸው፤ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ የምረጡኝ የቅስቀሳ ዘመቻዎች የዜጎችን የምርጫ ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ፣ ዜጎች ላመኑበት የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት ድምጻቸውን እንዲሰጡ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ሂደቱ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።