ቀጥታ፡

ለፆታ እኩልነትና ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚሰራ ፓርቲን ለመምረጥ ተዘጋጅተናል- ሴቶች

ጎንደር ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ለፆታ እኩልነትና ለሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚሰራ ፓርቲን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የጎንደር ከተማ ሴቶች ገለጹ፡፡

በዞኑ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ እየወሰዱ መሆኑ ይታወቃል።

ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሪት ፍቅረማርያም ሽፈራው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምርጫ የአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫና የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጫ መሳሪያ ነው።


 

አሁን ላይ በመገናኛ ብዙሃን የሚካሄዱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ለየትኛው ፓርቲ ድምፄን መስጠት  እንዳለብኝ  አስቀድሞ  ግንዛቤ እንዳገኝ እየረዳኝ ነው ብለዋል።

የጾታ እኩልነትን የሚያረጋግጥና ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጁና ቁርጠኛ የሆነ ፓርቲን ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ጥሩዬ ማሞ ናቸው፡፡


 

ሕገ-መንግስቱ የሰጠኝን ዴሞክራሲያዊ መብት በመጠቀም ይጠቅመኛል ላልኩት ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት የሚያስችለኝን ካርድ ወስጃለሁ ነው ያሉት።

ወይዘሮ ፌቨን ገዳሙ በበኩላቸው፤ የአንድ ሰው ድምጽ ዋጋ እንዳለው በመገንዝብ የመምረጥ መብትን የሚያጎናጽፈኝን የመራጭነት ካርድ አውጥቻለሁ ብለዋል፡፡ 


 

በአሁኑ ወቅትም ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን በሚያካሄዱት የምርጫ ቅስቀሳ ላይ የሚያስተላልፏቸው መልእክቶች ህዝቡ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲያካሂድ ግንዛቤ የሚፈጥር ነው ብለዋል።፡

ምርጫው በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰላማዊ ፍትሃዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን ለማበርከት ተዘጋጅተናል ሲሉም አስተያየት ሰጪዎቹ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም