በገጠር ኮሪደር ልማት እየተገነቡ የሚገኙ ሞዴል ቤቶች የአኗኗር ዘይቤያችንን ቀይረዋል - ነዎሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በገጠር ኮሪደር ልማት እየተገነቡ የሚገኙ ሞዴል ቤቶች የአኗኗር ዘይቤያችንን ቀይረዋል - ነዎሪዎች
ሐረር ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በገጠር ኮሪደር ልማት እየተገነቡ የሚገኙ ሞዴል ቤቶች የአኗኗር ዘይቤያቸውን መቀየር እንዳስቻላቸው የሐረሪ ክልል ነዎሪዎች ተናገሩ።
በክልል ከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ጽዱ እና ምቹ ከተሞችን እየፈጠረ ነው
በክልሉ በሁሉም ገጠር ወረዳዎች በኮሪደር ልማት መርሃ ግብር የሚገነቡ ሞዴል መንደሮችን የማስፋት ስራ እንደሚከናወንም የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር ገልፀዋል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች እንዳሉት በክልሉ በገጠር ኮሪደር ልማት የተገነቡ ቤቶች ዘመናዊ አኗኗር እንድንከተል እያደረገ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሶፊ ወረዳ ቡርቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጀማል በከር እንዳሉት፤ በአካባቢያቸው የተገነባው የኮርደር ልማትና ሞዴል መንደር አካባቢውን ከማስዋቡ ባለፈ፤ ከቀድሞ የተለየ የአኗኗር ዘይቤ እንዲጀምሩ አድርጓል።
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የክልላቸውን አመራሮች አመስግነዋል።
ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ አብዱረኡፍ አደም በበኩላቸው፤ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ ለኑሮ ምቹ የሆነ ከባቢን በመፍጠር ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ነው የሚገልጹት።
መንግስት የገነባልን ሞዴል መንደር አካባቢውን ውብ አድርጎታል፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋራም እዚህ ተገናኝተን አብርን በማሳለፋችን ደስ ብሎናል ብለዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ለኢዜአ እንዳሉት፤በክልሉ የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ በመቀየር የተሻለ ህይወት እንዲመራ የሚያስችለው የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም በከተማው በኮሪደር ልማት የተከናወኑ የመንገድ ግንባታ ስራዎችን ከገጠሩ ጋር የማስተሳሰር ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አንስተዋል።
በተለይም በክልሉ ሶፊ ወረዳ ቡርቃ ቀበሌ የተከናወኑት የገጠር ኮሪደር ሞዴል ቤቶች በአነስተኛ ወጪና በአካባቢው በሚገኙ ቁሶች ሞዴል የመኖሪያ ቤት እንደሚገነባ ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በቀጣይ ሶስት ወራት በገጠር ኮሪደር ልማት 250 ቤቶችን በመገንባት ሞዴል መንደሮችን የማስፋት ስራ ይከናወናል ብለዋል።
የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገውና በተሰባሰበ መልኩ በሚከናወነው ሞዴል መንደርን የማስፋት ስራ ከመንግስት ባለፈ ነዋሪውን ባሳተፈ መልኩ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ ቀደማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ሌሎች የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች የሐረሪ ክልልን መጎብኘታቸው ይታወሳል።