በክልል ከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ጽዱ እና ምቹ ከተሞችን እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልል ከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ጽዱ እና ምቹ ከተሞችን እየፈጠረ ነው
አዳማ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ፅዱ እና የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ የሚያስችሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ።
የኮሪደር እና መልሶ ማልማት አነስተኛ ቢዝነሶችን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ለስራ እና ለሸማቹ ሳቢ በሆነ መንገድ መልሶ በመገንባት የተሰራ ነው
ከልማቱ ጎን ለጎንም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመዘርጋት ስራም እየተከናወነ መሆኑ ተመላክቷል።
የሲዳማ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ሰለሞን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግሥት ከተሞች የብልጽግና ማሳያ እንዲሆኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የክልሉ ከተሞች ትርጉም ባለው መልኩ እንዲለሙ ትኩረት ተሰጥቷል።
በሀዋሳ ከተማ የተጀመረውን ውጤታማ የኮሪደር ልማት ስራ በክልሉ በሚገኙ ሌሎች ከተሞች ለማስፋፋት ታቅዶ ውጤታማ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በከንቲባ በሚመሩ ይርጋለም፣ በንሣ ዳዬ፣ አለታ ወንዶ፣ ወንዶ ገነት፣ ለኩ እና አለታ ጭኮ ከተሞች በፌዴራልና በክልል መንግሥት በጀት ልማቱ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሀገረ ሰላም፣ ጠጢቻ፣ ቦና እና መጪሻን ጨምሮ ከ60 በላይ አነስተኛ ከተሞች በአቅማቸው ልክ ወደ ኮሪደር ልማት ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማቱ የአስፓልት መንገዶች፣ ስማርት የኤሌክትሪክ ፖሎች፣ ምቹ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ የመዝናኛ ፓርኮች እና አረንጓዴ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አቶ ብሩክ አክለውም፣ በሀዋሳ ከተማ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ስድስት ተጨማሪ ከተሞች ለማስፋፋት የህንጻ ግንባታ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙራድ ከድር በበኩላቸው፤ ወልቂጤ አንጋፋ የንግድ ኮሪደር ብትሆንም ከቆይታዋ አንጻር ሳትለማ መቆየቷን ጠቅሰው፣ አሁን ላይ ግን ከተማዋን ለማዘመን 25 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደት 7 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ መከናወኑን ጠቅሰው ይህም የእግረኛ መንገዶችን የማስዋብ፣ ስማርት ፖል፣ የብስክሌት መንገድ እና የሕፃናት መዝናኛዎችን ያካተተ ነው ብለዋል።
ሁለተኛው ምዕራፍ 15 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለማካሄድ የዲዛይን ሥራ ተጠናቆ ተቋራጭ የመለየት ሂደት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል።
ይህ ልማት ከተማዋን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ተመራጭ ከማድረጉ ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ከንቲባው ገልጸዋል።
በተጨማሪም አገልግሎትን ዲጂታላይዝ ለማድረግና የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ግንባታ ለመጀመር የቦታ ልየታ መጠናቀቁን አረጋግጠዋል።